
ባሕር ዳር: መስከረም 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የተሟላ ዕውቀት እና ክህሎት ያለው፣ በመልካም ሥነ ምግባር የታነጸ፣ በማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች ተፈላጊ ውጤት ማምጣት የሚችል ትውልድ ለመፍጠር የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ ነው።
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ ደግሞ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል እና ምቹ የመማር ማስተማር አካባቢን መፍጠር አንዱ ነው።
በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከተከናወኑ ተግባራት ውስጥ የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ይገኝበታል። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ተገንብተው ወደ መማር ማስተማር በገቡ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ተወዳዳሪ እና ውጤታማ ተማሪዎችን ማፍራት ተችሏል።
የክልሉን የትምህርት ጥራት ይበልጥ ለማሻሻል ተጨማሪ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በክልሉ መንግሥት የግንባታ ሂደት ላይም ይገኛሉ።
በክልል እየተገነቡ ከሚገኙ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የፍኖተ ሰላም ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ይገኝበታል። ትምህርት ቤቱ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት በሁለት ምድቦች እየተገነባ ይገኛል። ግንባታው በ13 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ነው። በውስጡ የመማሪያ ክፍል፣ የተማሪዎች ማደሪያ፣ የመመገቢያ አዳራሽ፣ ቤተ መጽሐፍት፣ የሻወር እና የመጸዳጃ ቤቶችን በሙሉ አካቶም የያዘ ነው።

የፍኖተ ሰላም ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ ተቆጣጣሪ መሐንዲስ ሙላት ገሰሰ ፕሮጀክቱ በሁለት ተቋራጮች እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አንደኛው የግንባታ ሥራ ተጠናቅቆ የቀለም፣ የወለል ንጣፍ፣ የአልሙኒየም እና የመስኮት ገጠማ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አንስተዋል። የመንገድ ሥራውም የአፈር ሙሌት እና የውኃ ማፋሰሻ ተጠናቅቆ አስፋልት ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸዋል።
ሁለተኛው የግንባታ ሂደት አሁን ላይ 75 በመቶ መድረስ ቢኖርበትም በተለያዩ ምክንያትች ማከናወን የተቻለው 28 በመቶ መኾኑን ነው የተናገሩት። ችግሩንም ለአሠሪ ተቋሙ በየጊዜው ማቅረብ መቻሉንም ገልጸዋል። አሁን ባለበት ደረጃ ከቀጠለ ግንባታው በውሉ መሠረት ሊጠናቀቅ እንደማይችልም አንስተዋል።
ግንባታው ጥር 21/2018 ዓ.ም ድረስ እንዲጠናቀቅ የዕቅድ ጊዜ ተቀምጦለታል ብለዋል። ተቆጣጣሪ መሐንዲሱ እንዳሉት ግንባታው በተቀመጠለት ጊዜ ፈጥኖ ማጠናቀቅ ካልተቻለ ግን ክልሉን ለተጨማሪ ወጭ ይዳርጋል ብለዋል። ተማሪዎችም በወቅቱ ገብተው እንዳይማሩ እንቅፋት እንደሚኾንም ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሲቪል ምሕንድስና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሚካኤል ንብረት በክልሉ በስድስት ምድቦች እየተገነቡ ከሚገኙ ሦስት ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የፍኖተ ሰላም አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ አንዱ መኾኑን ገልጸዋል።
ግንባታው በሁለት ክፍሎች አየተከናወነ እንደሚገኝ የገለጹት ዳይሬክተሩ አንደኛው የግንባታ ሂደት እስከ የካቲት/2018 ዓ.ም ድረስ እንዲጠናቀቅ አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል።
ሁለተኛው የግንባታ ሂደት በሦስተኛ ወገን፣ በተቋራጩ የአሥተዳደር እና የአቅም ችግር ምክንያት በመጓተቱ ተጨማሪ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችልም ገልጸዋል።
አሁን ላይ ችግሮቹ መቀረፋቸውን ያነሱት ዳይሬክተሩ በቀጣይም ቀሪ ሥራውን በፍጥነት አጠናቅቆ ወደ ሥራ እንዲገባ ይደረጋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!