የመድኃኒት አቅርቦት አገልግሎትን ለማዘመን የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ።

7

አዲስ አበባ: መስከረም 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮ ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ስማርት የዲጂታል ጤና አቅርቦት ሰንሰለት ለማዘመን የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ በዋናነት በመላ ሀገሪቱ የመድኃኒት እና የሕክምና ዕቃዎች ፍሰትን የሚያቀላጥፍ ዘመናዊ፣ አስተማማኝ እና በመረጃ የተደገፈ የአቅርቦት ሰንሰለትን ለመንደፍ እና ለመዘርጋት ያለመ ነው ተብሏል።

ስምምነቱን የኢትዮ ቴሌኮም የቴክኖሎጂ ቺፍ ኦፊሰር ታሪኩ ደምሴ እና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ ተፈራርመዋል።

በመድረኩ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ኅብረተሰቡን በማገልገል ሂደት ፖሊሲዎችን በመቀየር አስቻይ ሁኔታን ለመፍጠር ሢሠራ መቆየቱን ተናግረዋል።

የዛሬው ስምምነትም ዘርፉ የጎደለውን በማየት አሠራርን ለማዘመን ወሳኝ ምዕራፍ የሚጀመርበት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ ተቋሙ አሠራሩን ወቅቱን የዋጀ በማድረግ ከወረቀት ንክኪ ነፃ አገልግሎትን እየተገበረ መቆየቱን ገልጸዋል።

የዛሬው ስምምነትም እንደሀገር የመድኃኒት አቅርቦቱን ዲጂታል በማድረግ ከሰው ንክኪ የፀዳ ለማድረግ እንደሚያግዝም ነው የጠቆሙት።

በዚህ የትብብር ማዕቀፍ ሁለቱ ተቋማት በመላ ሀገሪቱ የመድኃኒት እና የሕክምና ዕቃዎች ፍሰትን የሚያቀላጥፍ ዘመናዊ፣ አስተማማኝ እና በመረጃ የተደገፈ የጤና አቅርቦት ሰንሰለትን በጋራ በመንደፍ ተግባራዊ የሚያደርጉ ይኾናል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም የቴክኖሎጂ ቺፍ ኦፊሰር ታሪኩ ደምሴ የዲጂታል አማራጩ በውስጡ አንድ ወጥ አሠራር እና ቁጥጥር፣ አፋጣኝ መረጃ እና የቅድመ አደጋ ማንቂያዎችን በመጠቀም ለሚከሰት አደጋ ቀልጣፋ ምላሽ ለመስጠት ያስችላል ብለዋል።

ይህም የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የንብረት ቆጠራ ሥርዓትን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ፤ ጠንካራ የሃብት ደኅንነት ቁጥጥር ለማድረግ እና የሕግ ተገዢነትን ለማረጋገጥ፤ ከግምጃ ቤት ጀምሮ እስከ ተጠቃሚው ያለውን የመድኃኒት ስርጭት የአገልግሎት ጥራትን እና ፍጥነትን ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ተብሏል፡፡

ዘጋቢ፦ቤተልሄም ሰለሞን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አካል ጉዳተኝነት ሕልምን እውን ከማድረግ አያግድም”
Next article“የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝብ የሕዳሴን ድል በሌሎች ልማቶች ለመድገም ተነስቷል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ