
ደባርቅ: መስከረም 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ2017 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ከወሰዱ የደባርቅ ከተማ ተማሪዎች መካከል ተማሪ አብርሃም ገብረ ሕይወት ከፍተኛውን ነጥብ አስመዝግቧል። የማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ተማሪ የኾነው ተማሪ አብርሃም 514 ውጤት ነው ያስመዘገበው።
ተማሪ አብርሃም በተፈጥሮ ምክንያት የእግር ጉዳት ያለበት ቢኾንም አካል ጉዳተኝነት ጠንክሮ ከመሥራት እና ሕልምን እውን ከማድረግ እንደማያግድ አስተያየቱን ለአሚኮ ገልጿል።
ለተሻለ ውጤት ለመብቃት ጊዜን በአግባቡ መጠቀም እና የንባብ ባሕልን ማዳበር እንደሚገባም አክሏል። በርካታ ተግዳሮቶች ቢኖሩም የዓላማ ጽናት እና የይቻላል መንፈስ ካለ ችግሮቹን ማለፍ እንደሚቻል አብራርቷል።
ትምህርት ሂደት በመኾኑ በቀጣይም ካሰበበት ደረጃ ለመድረስ ጠንክሮ እንደሚሠራ ገልጿል።
የተማሪ አብርሃም ወላጅ እናት ወይዘሮ ማርዬ ዘውዱ ልጆች ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ የወላጅ ሚና ከፍተኛ መኾኑን የግል ተሞክሯቸውን ዋቢ አድርገው ተናግረዋል።
አካል ጉዳተኛ ልጆች ያሏቸው ወላጆች ለልጆቻቸው አስፈላጊውን ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ ለውጤት ማብቃት እንደሚችሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
መምህራንም በበኩላቸው ተማሪ አብርሃም አካል ጉዳተኝነቱ ሳይበግረው ለዚህ ውጤት መብቃቱ ለሌሎችም አርዓያነት ያለው ተግባር መኾኑን ገልጸዋል። መልካም ሥነ ምግባሩ እና ጠንካራ የንባብ ባሕሉ ለዚህ ውጤት እንዲበቃ አስተዋጽኦ እንዳደረጉለት አብራርተዋል።
በቀጣይ የሚኖረው የሕይወት ጉዞ የተቃና እንዲኾን ክትትል እና ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።
የደባርቅ ከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፈረደ ይትባረክ በ2017 በጀት ዓመት ተማሪዎችን ለተሻለ ውጤት ለማብቃት የተለያዩ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል። ተግባራቱ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አክለዋል።
የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን ለውጤት ለማብቃት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አብራርተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን