
አዲስ አበባ፡ መስከረም 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገራቸውን ለማገልገል በሥራ ቦታቸው ላይ እንዳሉ የተሰውትን የዶክተር አንባቸው መኮንንን ራዕይን ለማስቀጠል በስማቸው ሀገር በቀል ፋውንዴሽን በ2012 ዓ.ም ተመሥርቷል።
የዶክተር አንባቸው መኮንን ፋውንዴሽን በመላ የሀገሪቱ ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍሎች ማኅበራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሲባል ነው የተመሠረተው።
ፋውንዴሽኑ ባለፉት ዓመታት በርካታ ፕሮግራሞችን ነድፎ ሢሠራ የቆዬ እና እየሠራ ያለ ነው። ዛሬ ደግሞ ለቀጣይ ዓመታት የሚያገለግል ስልታዊ ዕቅድ እና ፕሮግራምን ይፋ አድርጓል።
የዶክተር አምባቸው መኮንን ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አሥኪያጅ መዓዛ አንባቸው ከአምስቱ ፕሮግራሞች ውስጥ አንዱ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን በፎገራ ወረዳ የሚተገበር እንደኾነ ገልጸዋል።
በወረዳው ያሉ የቆዳ የእጅ ሥራ ጥበብ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የማኅበረሰብ ከፍሎችን የሥራ ሕይዎት የሚያቀል ድጋፍ ተግባራዊ እንደሚደረግም ነው የተናገሩት።
በተለይ ሥራቸውን የሚያቀሉ ቴክኖሎጅዎችን በማቅረብ ከጎጆ ኢንዱስትሪ ወደ ኢንዲስትሪ እንዲገቡ የሚያደርግ መኾኑን ገልጸዋል።
ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸውም ተጓዳኝ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል ድጋፍ ይደረጋል ነው የተባለው። ፕሮግራሙ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚተገበርም ታውቋል።
በዕለቱ የተዋወቁት አምስት ስልታዊ ዕቅዶች በቀጣይ በመላ ሀገሪቱ የማኅበረሰብ አቀፍ ፕሮግራሞችን ለመተግበር የሚያስችል መኾኑንም አስገንዝበዋል።
በተለይ ሴቶች፣ ሕጻናት፣ ወጣቶች ላይ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በሰላም እና ደኅንነት ላይ በትኩረት እንደሚሠራም ነው የፋውንዴሽኑ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ያብራሩት።
ዶክተር አንባቸው መኮንን በሕይዎት በነበሩባቸው ጊዜ ይዘዋቸው የነበሩትን ማኅበረሰብ አቀፍ ፕሮግራሞችን ለማሳካት ዓለማቀፍ፣ የሀገር ውስጥ ተቋማት እና መላው ኢትዮጵያውያን ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦አዲሱ ዳዊት
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!