የጸጥታ አካላት አላማ እና ግብ የሕዝብን እና የሀገርን ደህንነት ማረጋገጥ ነው።

13

ሁመራ: መስከረም 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በፖሊስ ተቋማት ላይ እየተሠራ ያለው የሪፎርም ተግባር የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።

ሪፎርሙን ወደ መሬት አውርዶ ተግባራዊ ለማድረግ ያግዝ ዘንድ የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የዞን የሥራ ኀላፊዎች እና በሪፎርሙ መሠረት ምደባ ከተደረገላቸው 80 የክፍል ኅላፊዎች ጋር የሪፎርም ማሻሻያ እና የትውውቅ መርሐ ግብር በሁመራ ከተማ አካሂዷል።

ሪፎርሙ ፖሊስ፣ ሚሊሻ እና ሰላም አስከባሪ የጋራ አደረጃጀት በመፍጠር የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንዲችሉ ያደርጋል ሲሉ የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ወለላው ተገኘ ተናግረዋል።

የሕዝቡን ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ ነው ያሉት ኮማንደር ወለላው ፤ አጠቃላይ የጸጥታ መዋቅሩ በእኔነት ስሜት ኀላፊነቱን እንዲወጣ ሪፎርሙን በአግባቡ መፈጸም ይገባል ብለዋል።

“የፌዴራል፣ የክልል እና የዞን የጸጥታ መዋቅሩ ዓላማ አንድ ነው፤ ይኸውም የሕዝብን እና የሀገርን ሰላም እና ደህንነት ማረጋገጥ ነው” ብለዋል። ለዚህ ደግሞ ከኀላፊነት ድርሻ ባሻገር በጥምረት መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

አዲሱ የፖሊስ ሪፎርም የፖሊስ አባላት ከአለባበስ ጀምሮ ሕዝብን በቅንነት ለማገልገል የሚያስችል መልካም ሥነ ምግባር እንዲላበሱ ያግዛል ያሉት ደግሞ የዞኑ ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ምክትል ኀላፊ እና የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ ተወካይ ጌታቸው ሙሉጌታ ናቸው።

ፖሊስ ራሱን በማሻሻል እና በማብቃት የሕዝብን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ከተልዕኮዎቹ መካከል አንዱ ነው ብለዋል። በዚህም በኀላፊነት የተመደበው የፖሊስ አባል በሙሉ በሄደበት አካባቢ ሁሉ ሁለንተናዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚጠበቅበትም አሳስበዋል።

የፖሊስ ተቋም ዓለም አቀፋዊ ስለኾነ የክልሉም ኾነ የዞኑ የፖሊስ አደረጋጀቶች፣ ሕዝብ የጣለባቸውን ኀላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዲችሉ ሪፎርም መደረጉን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ዋኘው ደሳለኝ ናቸው።

በዚህ ሪፎርም መሠረት ኀላፊነት የተቀበሉ የፖሊስ አባላት ራሳቸውን በማብቃት እና በማሠልጠን የሕዝቡን ሁለንተናዊ ጥያቄዎች መፍታት ለማስቻል መሥራት እንዳለባቸውም አመላክተዋል።

ዞኑ የወሰን እና ማንነት ጥያቄው መልስ ያላገኘ ነው፤ በመኾኑም ሪፎርሙ ይዞት የመጣውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በትጋት ለመሥራት ዝግጁ ነን ሲሉ ተሳታፊ የፖሊስ አባላት ለአሚኮ ተናግረዋል።

የፖሊስ አባላት ባላቸው ልምድ፣ እውቀት እና ብቃት ማኅበረሰቡን ማገልገል እንዲችሉ የሪፎርሙ ሚና ከፍተኛ እንደኾነም ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል።

በዞን እና በወረዳ ደረጃ የፖሊስ አዛዥ ኀላፊነትን የተቀበሉ አባላት ቃለ መኀላ ፈጽመዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሕዳሴ በደም የከበረ፣ በላብ የታሰረ ነው።
Next articleየዶክተር አንባቸው መኮንን ፋውንዴሽን የአምስት ዓመት ስልታዊ ዕቅድ ይፋ አደረገ።