“ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በቂ ማብራሪያ ሰጥታለች” ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

15

አዲስ አበባ፡ መስከረም 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ የሕዳሴ ግድብ መመረቅ ኢ ፍትሐዊ የነበረውን የውኃ አጠቃቀም ትርክት ቀይሮታል ብለዋል። የዓባይ የውኃን አጠቃቀም ወደ ፍትሐዊ አቅጣጫ የቀየረ መሆኑንም ተናግረዋል።

ግድቡ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አቅም በመጨመር ተደማጭነትን የሚያሳድግ ነው ብለዋል በመግለጫቸው።

በአዲስ አበባ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተከናወኑ የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ እና የአፍሪካ ካረቢያን ማኅበረሰብ ጉባኤዎች የኢትዮጵያን አጀንዳ ቀራጭነት ከፍ ያለበት እና አዳዲስ ግንኙነቶች የተመሰረቱበት መሆኑንም ጠቅሰዋል ።

ኢትዮጵያ በቀጣይ በሚካሄደው 80ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ በመሳተፍ መስራች የሆነችበትን እና ለባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ እድገት ያደረገችውን አስተዋፅኦ ታካፍላለች።

በዚህም ባለፉት ወራት በሀገሪቱ ውስጥ የተደረጉ ስብሰባዎች ውጤቶችን ለመንግሥታቱ ድርጅት ታቀርባለች ብለዋል።

ግብፅ ለፀጥታው ምክር ቤት ስለሕዳሴ ግድብ ያስገባችውን ክስ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ቃል አቀባዩ ኢትዮጵያ ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም እንዲከበር እና ፍትሐዊ የመልማት ፍላጎት ብቻ ነው ያላት ብለዋል። “የኢትዮጵያ ጥያቄ እና ፍላጎት ተገቢ ስለመኾኑም ለለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በቂ የጽሑፍ ማብራሪያ አስገብተናል” ብለዋል።

የባሕር በርን በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄም “ኢትዮጵያ ሰላማዊ በኾነ መልኩ ነው የባሕር በር ጥያቄ እያቀረበች ያለችው፤ የባሕር በር ጥያቄ ለምን እንደሚያስፈልጋት የምናውቀው እኛ እንጂ ከውጭ ምላሽ የሚሰጡ አካላት አይደሉም” ብለዋል። በዚህም ብዙ ወዳጆች የኢትዮጵያ ጥያቄ ተገቢ መሆኑን እያመኑበት ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፍርድ ቤት መጥሪያ አቀባበልና ተጠያቂነቱ
Next articleሕዳሴ በደም የከበረ፣ በላብ የታሰረ ነው።