
ባሕር ዳር: መስከረም 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በርካታ ሰዎች መጥሪያ ለምን እንደሚሰጥ፣ በማን እንደሚሰጥ እንዲኹም መጥሪያውን ተቀብሎ አስፈላጊውን መረጃ ለፍትሕ ተቋማት በመሥጠት በኩል በውል ያለመረዳት ውስንነቶች ይስተዋላሉ።
አንዳንዴም ድንጋጤ፣ ፍርሃት ወይም በተቃራኒው ደግሞ ግድ የለሽነት፣ ቸልተኝነትና ለጉዳዩ ትኩረት ያለመስጠት ይታያል። “ሕግ አለማዎቅ ከተጠያቂነት አያድንም” ነውና ብሂሉ ስለ መጥሪያ ምንነት፣ በማን ይሰጣል? ለምን ይሰጣል? እንዴት ይሰጣል? አለመቀበል እና በመጥሪያው መሠረት አለመቅረብ ምን ያስከትላል?
👉መጥሪያ ምንድን ነው?
መጥሪያ በፍትሕ ተቋማት አሠራር አንዱ ሕጋዊ ሰነድ ነው። በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የፍትሐብሔር ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ቢራራ ወርቁ እንደገለጹት መጥሪያ አንድ ሰው በፍርድ ቤት ቀርቦ የሚፈለገውን መረጃ እንዲያስረዳ የሚሰጥ ሰነድ ነው።
መጥሪያ ለማንኛውም ሰው ሊሠጥ የሚችል እና በሕግ የሚፈለግ አካል ጥሪውን አይቶ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ የሚሠጥ ትዕዛዝ ስለመኾኑም አቶ ቢራራ ይገልጻሉ።
መጥሪያ የሚሰጠው ሰው ተከሳሽ ከኾነ የተከሰሰበትን ጉዳይ አውቆ፣ ፍርድ ቤት ቀርቦ የተጠየቀውን ነገር በአካል ተገኝቶ እንዲያስረዳ የሚደረግበት መንገድ መኾኑን የሕግ ባለሙያው አብራርተዋል። በተመሳሳይ ምስክር በፍርድ ቤት ቀርቦ እንዲያስረዳም መጥሪያ ለምስክሮች እንዲደርስ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
👉 ከፍርድ ቤት በምን መንገድ ወጭ ይደረጋል?
በፍርድ ቤት አሠራር ተከሳሽ የተከሰሰበትን ጉዳይ አውቆ እንዲቀርብ ለማድረግ እና ምስክር ደግሞ እንዲያስረዳ ለተከሳሽ ወይም ለምስክሮች ወጭ ይደረጋል።
ስለ መጥሪያ ይዘት በፍትሐ ብሔር ሕጉ የተቀመጠው መጥሪያ ላይ ጉዳዩ ተዘርዝሮ መቅረብ እንዳለበት በፍትሐ ብሔር ሕጉ ቁጥር 233 ተቀምጧል፡፡
በዚህም መሠረት ፍርድ ቤት የሚያዘጋጀው የመጥሪያ ይዘትም የክሱን ሁኔታ፣ የሚቀርብበት ቀን፣ ተከሳሹ ወይም ምስክር የሚቀርብበትን ፍርድ ቤትና ችሎት፣ ፍርድ ቤቱ ለምን ጉዳይ እንደፈለገው፣ መልሱን ይዞ እንዲመጣ የሚገልጽ ነው።
ተከሳሽም ይሁን ምስክር ስለሚጠየቀው ጉዳይ የተሟላ መረጃ ይዞ እንዲቀርብ የሚደረግበት መንገድ ስለመኾኑ ነው የሕግ ባለሙያው ያስረዱት።
👉መጥሪያ እንዴት ይደርሳል?
መጥሪያ ከፍርድ ቤት ወጭ ከተደረገ በኋላ በቀጥታ ለተከሳሹ መድረስ እንዳለበት አስገዳጅ ኾኖ በፍትሐ ብሔር ሕጉ ተቀምጧል።
መጥሪያው ለተከሳሽ በቀጥታ ለራሱ መስጠት፤ ይህ ካልተቻለ ደግሞ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ከቁጥር 96 እስከ 110 ላይ የተመለከቱትን የመጥሪያ አሰጣጥ ዘዴዎችን በመጠቀም መጥሪያው ለተከሳሽ መድረስ እንደሚኖርበት ተመላክቷል፡፡
በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 102 እንደተደነገገው መጥሪያ ሰጭው ለተከሳሽ፣ ለጠበቃው፣ ለወኪሉ ወይም መጥሪያውን ለመቀበል አግባብ ለኾነ ሰው በሚሰጥበት ወቅት ተቀባዩ የደረሰው ስለመኾኑ መፈረም ይጠበቅበታል፡፡
በዚህ መንገድ ማግኘት ካልተቻለ ግን እንደተከሳሹ ባህሪ ለተከሳሹ ቅርብ በኾኑ ሰዎች በኩል እንዲደርሰው ይደረጋል። በዚህ መንገድም ማግኘት ካልቻለ ከሳሹ አቤቱታውን ለፍርድ ቤቱ ድጋሚ በመሀላ ማቅረብ እንደሚችል አቶ ቢራራ አመላክተዋል።
ፍርድ ቤቱም ኹኔታውን አይቶ የመጨረሻው አማራጭ በጋዜጣ ላይ ጭምር ጥሪ እንዲተላለፍ ማድረግ ይችላል። ተከሳሹ በአማራጩ ካልቀረበ ግን በሌለበት ታይቶ ፍርድ ሊሰጥ እንደሚችል ነው ያስረዱት::
👉መጥሪያ ስለመቀበል ግዴታ
መጥሪያ ተቀባዩ የተቀበለበትን ቀን፣ ሲቀበል የነበሩ እማኞች ማስፈረም ይጠበቅበታል፡፡ ተቀባዩ መጥሪያውን ስለመቀበሉ የፈረመበት እና ራሱ ያረጋገጠበትን ለፍርድ ቤቱ እንደሚመለስ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 104 ይደነግጋል፡፡
መጥሪያ የተላከለት ተከሳሽ ወይም ምስክር መጥሪያውን የመቀበል ግዴታ አለበት። “አልቀበልም” በማለት ከሳሽን መግጠም የለበትም። ከሳሾችም በግዳጅ “ውሰድ፣ ተቀበል” ማለት አይጠበቅባቸውም። ተከሳሽ ወይም ምስክር አልቀበልም ስለማለቱ ሁለት እማኝ ይዞ በቃለ መሀላ አረጋግጦ ለፍርድ ቤቱ ማቅረብ ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
ፍርድ ቤቱም ይህንን አረጋግጦ ጉዳዩ በሌለበት እንዲታይ ይደረጋል። የምስክሮች ቃል የግድ አስፈላጊ ኾኖ ከተገኘ ታስሮ ሊቀርብ እንደሚችል የሕግ ባለሙያው አብራርተዋል።
የሕግ ባለሙያው እንደገለጹት ግዴታ ያለበት ተከሳሽ ብቻ ሳይኾን ከሳሽ ጭምር መኾኑን ያነሳሉ። ከሳሽ መጥሪያውን ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት የማድረግ ግዴታ አለበት። በከሳሽ ቸልተኝነት ያለ በቂ ምክንያት መጥሪያው አለመድረሱ ከተረጋገጠ ክሱን ፍርድ ቤት ሊዘጋው እንደሚችልም ጠቁመዋል።
ቀላል የኾኑ ወንጀሎችም ላይ የግድ መጥሪያ እንዲደርስ ጥረት ይደረጋል፣ የደረሰው ግለሰብ ካልተገኘ ክሱ ተቋርጦም ሊቆይ ይችላል ነው ያሉት።
ከፍተኛ ውሳኔ ማለትም ከ12 ዓመት በላይ የእስር እና ሞት የሚያስወስኑ ከኾኑ በጋዜጣ ተጠርቶ እንዲመጣ ይደረጋል። ካልመጣ ግን ጉዳዩ በሌለበት ተወስኖ በተገኘበት ጊዜ ፍርዱ ተፈጻሚ እንደሚኾን ባለሙያው አብራርተዋል።
በፍትሕ ሥርዓቱ በተከሳሽም ይኹን በከሳሽ በኩል ተገቢው ፍትሕ እንዲረጋገጥ መጥሪያ አንዱ መሠረታዊ ጉዳይ በመኾኑ መጥሪያ በትክክለኛው መንገድ ማድረስ አስፈላጊ ነው።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!