
ባሕር ዳር: መስከረም 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እምቅ አቅም ካላቸው ሀገራት ውስጥ ትጠቀሳለች። ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች ውስጥም ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የግብርና ምርት ነው።
ከምታመርታቸው የግብርና ምርቶች ውስጥ በርበሬ አንዱ ነው። በኢትዮጵያ በዚህ ምርት የሚታወቁ በርካታ አካባቢዎችም ይገኛሉ። በርበሬ ምርት ከሚታወቁ የኢትዮጵያ አካባቢዎች መካከል የአማራ ክልል አንደኛው ነው።
ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በየዓመቱ ከ76 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበርበሬ ይሸፈናል። በሄክታር ከ18 እስከ 20 ኩንታል ምርት ይገኛል።
👉የበርበሬ ምርት እና የምዕራብ ጎጃም ዞን አካባቢ
የአማራ ክልል የበርበሬ አምራች ከኾኑት ዞኖች መካከል የምዕራብ ጎጃም ዞን አንዱ ነው። በዞኑም ወንበርማ፣ ቡሬ ዙሪያ ወረዳ፣ ጃቢ ጠህናን እና ደንበጫ ወረዳዎች በስፋት በርበሬ በማምረት ተጠቃሽ ናቸው።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ አግማስ አንተነህ እንደገለጹት በዞኑ 21 ሺህ 980 ሄክታር መሬት በበርበሬ ምርት ይሸፈናል። ከዚህ ውስጥ 17 ሺህ 940 ሄክታሩ በኩታ ገጠም የሚለማ ነው ብለዋል።
በርበሬ አዋጭ እና ገበያ ላይ ተፈላጊ በመኾኑ በኪሎ ግራም እስከ 700 ብር እየተሸጠ መኾኑን ተናግረዋል። ይህ ከፍተኛ ዋጋ የአካባቢውን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ በማድረግ ኑሯቸውን እንዲለውጡ እና ሃብት እንዲያፈሩ እየረዳቸው መኾኑንም አክለዋል።
👉የበርበሬ ምርት ፈተናዎች እና መፍትሔዎች
ምንም እንኳን በርበሬ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ቢኾንም በምርቱ ላይ የሚከሰት በሽታ ዋናው ስጋት ኾኖ ቀጥሏል።
በሽታው ሰብሉን ካጠቃው ኪሳራ የሚያስከትል በመኾኑ አንዳንድ አርሶ አደሮች ከበርበሬ ምርት ይወጣሉ። ለበሽታው የተሻለ መድኃኒት አለመኖሩም ሌላው ችግር ነው።
ይህን ችግር ለመፍታት የግብርና ባለሙያዎች በሽታው ከመከሰቱ በፊት ሰብል ማፈራረቅ፣ የተመረጡ ዘሮችን መጠቀም እና የተለያዩ የመከላከያ ሥራዎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ተገልጿል።
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የመስኖ እና ሆርቲካልቸር ልማት ዳይሬክተር ይበልጣል ወንድምነው እንዳሉት ለበርበሬ አምራች አርሶ አደሮች በተባይ ቁጥጥር እና አሰሳ ዙሪያ ሥልጠና ከመስጠት በተጨማሪ የገበያ ትስስርም እየተፈጠረላቸው ነው።
👉የበርበሬ ተሻሻለ ዝርያ እና የወደፊት ዕቅዶች
በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛው እየለማ ያለው “ማረቆፋና” የተባለ የበርበሬ ዝርያ ነው። ይህ ዝርያ አካባቢውን በመላመድ ምርታማነቱ ከፍተኛ እና ለገበያም ተፈላጊ መኾኑ ተገልጿል።
በአማራ ክልል በዚህ ዓመት ከ75 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበርበሬ ተሸፍኗል። በቀጣዩ የምርት ወቅት ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የበርበሬ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ ደግሞ በክልሉ የሚታየውን የበርበሬ ዋጋ ንረት ለመቀነስ እና ምርቱ ከክልሉ አልፎ በሀገር ደረጃ ኢኮኖሚውን በመደገፍ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ተጠቅሷል።
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!