
ደብረ ማርቆስ፡ መስከረም 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ2012 ዓ.ም ተማሪዎችን ተቀብሎ የማስተማር ሥራ የጀመረው የክቡር ዶክተር ሐዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በ2017 ዓ.ም 25 ተማሪዎችን በተፈጠሮ ሳይንስ ትምህርት ለሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና አስፈትኗል፡፡
ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቱ ያስፈተናቸውን ሁሉንም ተማሪዎች አሳልፏል። 24 ተማሪዎች ደግሞ ከ529 በላይ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡
ተማሪ አራጋው ሹመት እና ተማሪ ሙሉየ ግርማ የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ናቸው። በሀገር አቀፍ ፈተናው ከ560 በላይ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡
ከተማሪዎች ጋር በኅብረት ማጥናታቸው እና በትምህርት ቤቱ መምህራን በዕውቀት እና በሥነ ልቦና ዝግጁ እንዲሆኾኑ መደረጉ ከፍተኛ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እንዳገዛቸው ገልጸዋል። በቀጣይ የሕክምና ሙያን በማጥናት ሀገርን ለማገልገል እንደሚፈልጉም ነው የተናገሩት።
በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ገብተው መማራቸው ትኩረታቸውን ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያደርጉ እና ጊዜያቸውን በአግባቡ ለመጠቀም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገላቸውም ገልጸዋል።
በክቡር ዶክተር ሐዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት የሂሳብ መምህር አወቀ ዘገየ የተማሪዎች የማወቅ ፍላጎት መኖር እና የትምህርት ቤቱ መምህራን ለተማሪዎች ያደርጉት የነበረው እገዛ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
የክቡር ዶክተር ሐዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት
ርእሰ መምህር ደረጀ ከፈለኝ ትምህርት ቤቱ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡን እና ሁሉንም ያስፈተናቸውን ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ማሳለፉን አብራርተዋል።
በትምህርት ቤቱ የተሟላ ግብዓት ባልተሟላበት እና በአካባቢው ያለውን የጸጥታ ችግር ተቋቁመው ይህን ውጤት ማስመዝገባቸው የሚያሥመሠግን ነው ብለዋል፡፡
የተመዘገበው ውጤት ወደፊት ለሚመጡ ተማሪዎች መነሳሳትን የሚፈጥር እና የትምህርት ጥራት እንዲመጣ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የክቡር ዶክተር ሐዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በቀጣይም ተማሪዎችን ተቀብሎ በተሟላ ሁኔታ እንዲያስተምር የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!