ተማሪዎችን በትምህርት ቁሳቁስ በመደገፍ ትውልድ የመገንባት ሀገራዊ ኀላፊነታችንን እንወጣ።

8
ባሕር ዳር: መስከረም 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ በጎ አድራጓት ማኅበር ከ1 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ተማሪወች የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል ።
አሕመድ ይማም የባሕር ዳር ከተማ በጎ አድራጎት ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ማኅበሩ በ37 የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ላይ ከ1 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ እንዳደረገ ነው የገለጹት።
በጎ ተግባሩ ሁሌም በየዓመቱ እንደሚቀጥልም ነው የተናገሩት። ድጋፎቹ በዋናነት በትምህርት፣ በጤና፣ በማዕድ ማጋራት እና በመኖሪያ ቤት ግንባታ ላይ እንደኾነም ሥራ አሥኪያጁ ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ.ር) የበጎ አድራጎት ማኅበሩ እንደ ሁልጊዜው ሁሉ ተማሪዎችን ለመርዳት አንድ ደርዘን ደብተር ለአንድ ተማሪ በማዘጋጀት ከነገ ሀገር ተረካቢ ተማሪወች ጎን መቆሙን ስላስመሰከረ እናመሰግናለን ብለዋል።
ማኅበሩ ትውልድን ለመቅረጽ ጥረት እያደረገ እንዳለ እና ሰዋዊነት የተላበሰ ተግባር እየሠሩ እንደኾኑም ገልጸዋል። የዚህ ድጋፍ መደረግ በመማሪያ ቁሳቁስ እጥረት የሚቀሩ ተማሪወችን ይቀንሳል ሲሉም ነው የተናገሩት።
በዕለቱ የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ “የነገ ሀገር ተረካቢ ተማሪወች ላይ መሥራት ሀገር መገንባት ነው” ብለዋል።
የተደረገው ድጋፍ ተማሪዎች በቁሳቁስ ችግር ምክንያት ከትምህርት ገበታ እንዳይርቁ ያደረገ እንደኾነም ነው የገለጹት። ተማሪዎች ቁሳቁስ ተሟልቶላቸው እንዲማሩ እና ለውጤት እንዲበቁ ያስቻለ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
የትምህርት ሥራ ትብብርን እንደሚጠይቅ ተገንዝበው ይህንን ድጋፍ ያደረጉ በጎ አድራጊዎችንም አመስግነዋል።
በበጎ አድራጎት ላይ የተሠማሩ ሌሎች አካላት፣ ተቋማት እና ግለሰቦችም አቅም የሌላቸውን ተማሪዎች በትምህርት ቁሳቁስ በመደገፍ ትውልድ የመገንባት ሀገራዊ ኀላፊነታቸውን መወጣት እንድችሉ ምክትል ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ: ሰመሀል ፍስሀ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሕዳሴ የአንድነት እና የኅብረ ብሔራዊነት ማሕተም ነው።
Next articleየምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ መልዕክት፦