
ባሕርዳር: መስከረም 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝባዊ የድጋፍ እና የደስታ መግለጫ ሰልፍ ተካሂዷል።
በኢትዮጵያውያን አንድነት እና ኅብረት የተገነባው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከተጠናቀቀ በኋላ ኢትዮጵያውያን ወደ አደባባይ እየወጡ ደስታቸውን እየገለጹ ነው።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝብም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን ተከትሎ ወደ አደባባይ በመውጣት ደስታውን ገልጿል።
ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በክልሉ በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ፣ በምዕራብ ኦሞ ዞን ጀሙ ከተማ፣ በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ፣ በኮንታ ዞን፣ በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።
በድጋፍ ሰልፉ በሕዳሴው ግድብ አይቻልም የተሰበረበት፣ በትብብር የሚያቅት እንደሌለ የታየበት ነው ተብሏል። የዜጎች እጅ ለእጅ ተያይዞ መነሳት ለዘመናት የዘለቀ የልማት ጥማትን መመለስ እንደሚቻል ሕዳሴ ማሳየቱም ተገልጿል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከልማት ባሻገር ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ ያስተሳሰረ፣ የጋራ አሻራ ያረፈበት፣ በብዝኃነት ውስጥ ጠንካራ አንድነትና የማይበጠስ ትስስር የፈጠረ ፕሮጀክት መኾኑም ተመላክቷል።
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት፣ ዕውቀት፣ ጉልበት እና ገንዘብ የተገነባ የነፃነት፣ የኩራት፣ የአይበገሬነት እና የስኬት ተምሳሌት ነው። አንፀብራቂ የጋራ ታሪክ ሐውልት ኾኗልም ተብሏል።
በራስ መተማመንን የሚያጎላ፣ ተምሳሌት እና ቀደምት ሀገር መሆናችን በአደባባይ ያስመሰከረ ነው። ሕዳሴ የአንድነት እና የኅብረ ብሔራዊነት ማሕተም ነው ተብሏል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!