
ደባርቅ: መስከረም 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎንደር ዞን ማረሚያ ቤቶች መምሪያ አብሮ ለመሥራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከዞኑ ፍትሕ መምሪያ ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ቢምረው ካሳ የሕግ ታራሚዎችን በሥነ ልቦና እና በሥራ ክህሎት ለማብቃት የሚደርገው ጥረት የሚበረታታ እንደኾነ ገልጸዋል።
ከፍትሕ ተቋማት ጋር በጋራ መሥራት መቻል የታራሚዎችን የሕግ ጉዳይ በቅርበት መከታተል እና ማሥፈጸም እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ማረሚያ ቤቶች መምሪያ ኀላፊ ዋና ኢንስፔክተር አበበ አዳነ ከፍትሕ ተቋማት ጋር በጋራ መሥራት ለሕግ ታራሚዎች አገልግሎት ውጤታማ ተግባራትን ለመከወን እንደሚያስችል ገልጸዋል።
የአሠራር ለውጥ መደረጉ ከሕግ ዕውቀት አንጻር የተገናዘበ ፍትሐዊ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝም አንስተዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ፍትሕ መምሪያ ኀላፊ ነጋ ሲሳይ የማረሚያ ቤት ተግባር እና የፍትሕ ተቋማት አገልግሎት ተመጋጋቢ በመኾናቸው የአሠራር ፍተሻ መደረጉ ተገቢ ነው ብለዋል።
የሕግ ታራሚዎችን የሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ የውሳኔ እና የፍርድ ሂደት ለማሻሻል እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!