
አዲስ አበባ: መስከረም 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን በማስመልከት በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።
የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች ዓባይ የዓመታት ቁጭታችን የተወጣንበት፤ በኅብረት የገነባነው የመቻላችን ምልክት ነው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስንተባበር የማንሠራው ታሪክ እንደሌለ ማሳያ ነው ብለዋል።
የአዳማ ከተማ ከንቲባ ኃይሉ ጀልዴ ዓባይ በባይተዋርነት ለዘመናት ማዕድን እና አፈር ሲያጉዝ እንደቆየ አንስተዋል። ታሪክ ሠሪ ትውልድ ለቁም ነገር እና ለልማት ውሏል ብለዋል።
በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን በመቋቋም የተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የምሥራቅ ሸዋ ዞን አሥተዳዳሪ አባቡ ዋቆ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የአብሮነት ምልክት ኾኖ የተሠራ እንደኾነ አንስተዋል። ጠላቶቻችን ከፋፍለው እንዳንሠራው ቢረባረቡም በአንድ ቆመን ሴራቸውን ያከሸፍንበት ነው ብለዋል።
በዚህ ፕሮጀክት የነበረንን አንድነት አጠናክረን በመቀጠል በቀጣይ ለታሰቡ ፕሮጀክቶች ስኬትም መትጋት ይገባናል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- አድሱ ዳዊት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!