
ፍኖተ ሰላም: መስከረም 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁን ተከትሎ ሕዝቦች ደስታቸውን በድጋፍ ሰልፍ ገልጸዋል።
በድጋፉ ላይ የተገኙት የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ጊዜው ደግአረገ ለበርካታ ዓመታት በጠላቶቻችን ሴራ ያለንን ሃብት እንዳንጠቀም የሃሰት ትርክት ሢሠራ ቢቆይም ይህን በመቀየር እና የሕዳሴ ግድቡን በማጠናቀቅ ትርክቱን መሻር ችለናል ብለዋል።
የብዙ ዓመታት ፍላጎት እና ምኞት የኾነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በማጠናቀቃችን ልንኮራ ይገባል ነው ያሉት።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዕድሜዓለም አንተነህ “ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአይችሉምን ትርክት የሰበረ የኩራታችን ምንጭ ነው” ብለዋል።
የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ሴራ የበጣጠሰ እና የነገ ማንሠራራታችንን ያመለከተ አርማችን መኾኑን ዋና አሥተዳዳሪው ገልጸዋል ።
በድጋፉ ላይ የተገኙት የፍኖተ ሰላም ከተማ ነዋሪዎች ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የረጅም ጊዜ የልማት ቁጭታችንን ያሳካንበት ነው ብለዋል። የውጭ ጫናዎችን በመቋቋም ለዚህ ስኬት በመብቃቱ ደስተኛ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
በሕዳሴ ግድቡ ላይ ያሳየነውን ተሳትፎ እና አንድነት መንግሥት ቀጣይ በሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች ላይ ለመድገምም ዝግጁ መኾናቸውን አረጋግጠዋል።
በሰልፉ ላይ የምዕራብ ጎጃም ዞን እና የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር መሪዎች እንዲሁም የፍኖተ ሰላም ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!