
ደባርቅ: መስከረም 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዳግማዊ ዓድዋ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመመረቁ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ ተካሄዷል።
ላለፉት 14 ዓመታት በግንባታ ላይ የነበረው የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመመረቁ ማኅበረሰቡ በነቂስ ወጥቶ ደስታውን ገልጿል።
በሰሜን ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አደራጀው ባዘዘው በዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የዘመናት ቁጭት እና ብሶት የወለደው ታሪካዊ ቅርስ መኾኑን ገልጸዋል።
የሕዳሴ ግድቡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራውን ያሳረፈበት እና በጽናት የታገለለት የጋራ ስኬት ምሳሌ ነው ብለዋል።
በሰልፉ የተሳተፉ የማኅበረሰብ ክፍሎችም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያንን የጽናት እና የአይበገሬነት ቀደምት ታሪክ ያስታወሰ እና ለዓለም ያስተዋወቀ ነው ብለዋል።
በጋራ የመፈጸም እና በአንድነት የመቆምን ስኬታማ ጉዞ የገለጠ እና ለቀጣይ ለሌሎች ሀገራዊ ሥራዎች መነሳሳትን የፈጠረ ነው ብለዋል።
በሰልፍ መርሐ ግብሩ አሚኮ ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶች በበኩላቸው የሕዳሴ ግድቡ የመተባበር እና በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በአንድነት የመቆም ውጤት ነው ብለዋል።
ሰላም የሁሉም መሠረት በመኾኑ ሰላምን ማጽናት እና የልማት አርበኝነትን መቀጠል እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በሰልፉ የተሳተፉ የደባርቅ ከተማ ወጣቶችም የሕዳሴ ግድቡ ተጠናቅቆ ለዚህ በመብቃቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
ሕዳሴ የኢትዮጵያውያን በተለይም የወጣቶች የነገ ብሩህ ተስፋ ማሳያ እንደኾነ አብራርተዋል። በቀጣይም የተገኘውን ሀገራዊ ስኬት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተመላክቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
