
ወልድያ፡ መስከረም 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ምልክት ነው” በሚል መሪ መልዕክት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን መመረቅን አስመልክቶ በወልድያ ከተማ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል።
የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ ባስተላለፉት መልዕክት ጠላት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስቆም ያሴረው ፖሊቲካዊ ሴራ ጠውልጓል ብለዋል።
ጠላቶች ከነተባባሪዎቻቸው የዘመናት ሴራቸው ጤዛ ኾኖ ረግፏል ነው ያሉት። ለዚህም ምክንያቱ የኢትዮጵያውያን ትብብር እና አብሮ መቆም እንደኾነ ነው የተናገሩት።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአፍሪካውያን ላይ የተንሰራፋውን የቅኝ ግዛት የሴራ ውል በመቅደድ ፍትሐዊ የተግባር ሰነድ ለመላው አፍሪካውያን የተበረከተበት እንደኾነም ነው የጠቆሙት።
የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ፍጻሜ ላይ መድረሱ ፋይዳው የኢኮኖሚ ማንሰራራት ብቻ ሳይኾን የጂኦ ፖለቲካ ጉዳይም ነው ብለዋል። የግድቡ መጠናቀቅ ለአሁኑ ብቻ ሳይኾን ለቀጣዩ ትውልድም መልካም ዕድል ነው ሲሉ አስረድተዋል።
በታላቁ የሕዳሴ ግድብ የተገኘውን ድል በሌሎች ታላላቅ የልማት ድሎች ለመድገም ዛሬም እንደ ትናንቱ መተባበር እና ሰላምን ማስከበር ግድ ይላል ነው ያሉት።
የሕዳሴ ግድብን ማሳካት እንደተቻለው ሁሉ ለቀጣዩ ትውልድ ወደብ አልባ ሀገር ማስረከብ አይገባም ነው ያሉት። ግለሰቦች የፈጠሩትን ታላቅ ስህተት ይህ ትውልድ ማረም እና ማስተካከል እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
