“ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የጠላቶቻችንን ሴራ ያመከንበት ታሪካዊ ፕሮጀክት ነው”

3

እንጅባራ: መስከረም 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመላው ኢትዮጵያውያን አሻራቸው ያረፈበት፣ የይቻላል መንፈስ ምልክት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከረጅም ዓመታት እልህ አስጨራሽ የግንባታ ሂደት በኋላ መቋጫውን አግኝቷል።

በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የእንጅባራ ከተማ ነዋሪዎችም የዚህ ታላቅ ፕሮጀክት በስኬት መጠናቀቅ የፈጠረባቸውን ደስታ በድጋፍ ሰልፍ ገልጸዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማሳያ ሐውልት መኾኑንም ሰልፈኞቹ ገልጸዋል።

ግድቡ ኢትዮጵያውያን በዓባይ ወንዝ ላይ ለነበራቸው የዘመናት ቁጭት የተከፈለ ካሳ እንደኾነም ሰልፈኞቹ አንስተዋል

የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ የኔዓለም ዋሴ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከ80 በመቶ በላይ የዓባይ ወንዝ ውኃ የምትጋራው ኢትዮጵያ የበይ ተመልካችነቷ ያከተመበት ታሪካዊ ፕሮጀክት ሲሉ ገልጸዋል።

ግድቡ መላው ኢትዮጵያውያንን በአንድነት ያስተሳሰረ፣ የአሸናፊነት ምልክት፣ የብልጽግናችን ማስፈንጠሪያ የአዲስ ዓመት ስጦታ እንደኾነም አንስተዋል።

በሰልፉ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የጠላቶቻችንን ሴራ ያመከንበት ታሪካዊ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

ግድቡ የአይበገሬነት፣ የአሸናፊነት እና የድል አድራጊነት ምልክት መኾኑንም ተናግረዋል።

ዓባይን በጋራ የመጠቀም ጉዳይ በቀደሙት አባቶቻችን ሲታሰብ የኖረ ግን ደግሞ በታሪክ አጋጣሚ በዚህ ትውልድ እውን የኾነ የሀገራችን ልማት ማሳለጫ ሞተር እንደኾነም ገልጸዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከቆሙ የማይበግራቸው ነገር እንደሌለ ማሳያ ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው በግድቡ ግንባታ ወቅት የታየው የኢትዮጵያውያን አንድነት እና መነሳሳት በሌሎችም ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ታሪካዊ ጠላቶቻችን ዓባይን እንደበረከት ሳይኾን እንደ እርግማን እንድናየው አድርገውን ኖረዋል”
Next articleሕዳሴ ለትውልድ ታላቅ ገድል ያቆምንበት ነው።