
ደሴ: መስከረም 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ እና መመረቅን ተከትሎ የቃሉ ወረዳ ነዋሪዎች የደስታ እና የድጋፍ ሰልፍ በደጋንና በገርባ ከተማ አድርገዋል።
አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡት የሰልፉ ተሳታፊዎች ሕዳሴ ግድብ ተመርቆ በማየታቸው እና የዚህ ታሪክ ተጋሪ በመኾናቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይ ሀገራችን የወጠነቻቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች ከግብ እንዲደርሱ ማንኛውንም አይነት ድጋፍ እና እገዛ ለማድረግ ወደ ኋላ እንደማይሉም አስገንዝበዋል።
የቃሉ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ሙህዲን አህመድ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ዓባይን እንደበረከት ሳይኾን እንደ እርግማን እንድናየው ለዘመናት የሠሩብን ትርክት እና የዲፕሎማሲ ጫና ተለውጧል። በአንድነት እና በጽናታችን ለፍሬ አብቅተነዋልና እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ሕዳሴ ግድብ የአንድነት፣ የመቻል እና የማንሠራራታችን መገለጫ ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው በቀጣይ የባሕር በር ጥያቄን ይዞ መንግሥት እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የወደብ ባለቤት የነበረች ሲኾን ይህን ታሪካዊ የወደብ ባለቤትነቷን ለማስመለስ በሰላማዊ መንገድ እየሠራች እንደኾነ አንስተዋል።
በአዲሱ ዓመት መንግሥት በርካታ ሰው ተኮር የኾኑ የልማት ሥራዎችን እና ሜጋ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ለመሥራት ያቀዱት ዋና አሥተዳዳሪው ለስኬቱም ሕዝቡ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ኡስታዝ ሼኽ አሊ ሙሃመድ በበኩላቸው ሕዳሴ ግድብን በብዙ ውጣ ውረድ መሙላት እና ማጠናቀቅ መቻላችን የአንድነታችን እና የትብብራችን ውጤት ነው ብለዋል።
በቀጣይ ሀገራችን ለወጠነቻቸው ታላላቅ ፕሮጀክቶች መሳካት እና ሰላምን ለማምጣት የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ሁሉ መክፈል ይገባናል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፡- መሃመድ በቀለ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
