
ገንዳ ውኃ: መስከረም 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁን አስመልክቶ “ኢትዮጵያ ችላለች” በሚል መሪ መልዕክት ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በገንዳ ውኃ ከተማ ተካሄዷል።
በራሳችን ልፋት እና በራሳችን ጥረት የገደብነው ሕዳሴው ግድብ የኩራታችን ምልክት ነው ሲሉ ሰልፈኞች ተናግረዋል።
ሕዳሴው ግድብ አንድነታችን፣ መተባበራችን እና ኅብረ ብሔራዊነታችን ያስተሳሰረ ታላቅ ፕሮጀክት ነው ሲሉ ሰልፈኞች ገልጸዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ለምርቃት በመብቃቱ ዳግም የተወለድን ያህል እንዲሰማን አድርጎናል ብለዋል።
ሕዳሴው ግድብ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾን ለአፍሪካውያንም የጀግንነት ተምሳሌት መኾኑን ሰልፈኞች አንስተዋል።
ቀጣይም በሚሠሩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ ድጋፋችን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አብዱልከሪም ሙሐመድ ሕዳሴው ግድብ የወል ትርክትን የሚያጠናክር እና ብልጽግናን የምናረጋግጥበት የማንሠራራት ምልክት መኾኑን ተናግረዋል። ግድቡ የጠላቶቻችን ሴራ ያከሸፍንበት እና አንገት ያስደፋንበት ነው ብለዋል።
ግድቡ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይኾን የአፍሪካ ሀገራትን የጋራ ተጠቃሚነትን የሚረጋገጥበት መኾኑን ከንቲባው አንስተዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እያሱ ይላቅ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የታሪክ ለውጥ ያመጣንበት፣ ዓለምን ያስደመመ እና የሕዝባችን ጥንካሬ በግልጽ ያሳየንበት ነው ብለዋል።
የአካባቢውን ሰላም በጋራ እያስከበርን ማኅበረሰቡን የልማት ተጠቃሚ እንዲኾን በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ዋና አሥተዳዳሪው አስገንዝበዋል።
በቀጣይ በሚተገበሩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ ሁሉም ማኅበረሰብ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
