
ደሴ: መስከረም 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የታላቁ የሕዳሴ ግድብ መመረቁን አስመልክቶ በደሴ ከተማ ታላቅ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄዷል።
ሁሉም ኢትዮጵያውያን ያለ ልዩነት የተሳተፉበት፣ በትውልድ ቅብብሎሽ እና በመሪዎች ቁርጠኝነት የተገነባው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በመመረቁ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ደስታቸውን በአደባባይ ገልጸዋል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ኢትዮጵያውያን በጋራ ኾነው በሕዳሴ ግድቡ ላይ አሻራቸውን በማስቀመጥ በትውልዱ የሚዘከር ተግባር አከናውነናል ብለዋል።
ግድቡ የሀገርን እና የሕዝብን የመቻል አቅም በተግባር ያሳየ የኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ከራስ ለራስ የሚበረከት ውድ ስጦታ እንደኾነ ገልጸዋል። በቀጣይም በሌሎች ታላላቅ ሀገራዊ ሥራዎች ለመሳተፍ ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የሃይማኖት አባቶች በበኩላቸው ዓባይ ለኢትዮጵያውያን መንፈሳዊ ቁርኝት እንዳለው ገልጸው ቀደም ባለው ጊዜ የሀገራችንን ለም አፈር እየጠረገ በመኮብለሉ ቁጭት ሲፈጥር እንደነበር ተናግረዋል።
ዛሬ ወደ ሀገራችን እንዲፈስ በመደረጉ የሕዳሴ ግድብን ከቦታው ድረስ ተገኝተው ለማየት ጉጉት እንዳደረባቸው ገልጸዋል። “ዓባይ ለእናት ሀገሩ ልማት ውሏል፤ የባሕር በር ጥያቄያችንም እንደ ግድቡ መልስ እንደሚያገኝ ፅኑ እምነት አለን” ነው ያሉት
በቁርጠኝነት በመሥራት ለዚህ እንዲበቃ ያደረጉ መሪዎችንም አመስግነዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ዓባይ ለወጣበት ማህፀን ተመልሶ ጥቅም እንዲሰጥ በመደረጉ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
“ሀገራችን በበርካታ የተፈጥሮ ፀጋዎች የታደለች ብትኾንም ታሪካዊ ጠላቶቻችን የተለያዩ ስልቶችን በመንደፍ እንቅፋት እየፈጠሩ ሳንጠቀምበት ቆይተናል” ብለዋል።
የዘመናት ቁጭት የፈጠረው የአርበኝነት ስሜት በማደጉ ተፈጥሮ የሰጠችንን ፀጋ ገንብተን እንድንጠቀም ችለናል ነው ያሉት።
አርበኛ እና ጀግና ሕዝብ ቢኖርም የሚያስተባብረው ጥበበኛ መሪ ያስፈልገዋል ያሉት ከንቲባው ዛሬን የምንኖረው ትናንት በሠራነው ስኬት ብቻ ሳይኾን ነገ በሰነቅነው ራዕያችን ጭምር እንደኾነ ተናግረዋል።
በቀጣይ የሚሠሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች እውን እንዲኾኑ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ከመንግሥት ጎን በመቆም በከተማዋ ሰላም፣ ልማት እና መልካም አሥተዳደር ተሳታፊ እንዲኾን ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ አንተነህ ፀጋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
