
ከሚሴ: መስከረም 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከሚሴ ከተማ “በኅብረት ችለናል” በሚል መሪ መልዕክት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ የዘመናት የቁጭት ጥያቄ የነበረውን የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አጠናቅቀን ችለን ለዓለም ያሳየንበት ታሪካዊ ወቅት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመላ ኢትዮጵያውያን አሻራ ምልክት ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው በኅብረት ስንቆም የማናሳካው ነገር የለም ብለዋል።
የሕዳሴ ግድብ እንዳይሳካ ከውስጥ እና ከውጭ የገጠሙንን ችግሮች ፀንተን በመቆም በጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ እና በሕዝባችን ትብብር ያሳካነው ነውም ብለዋል።
ሀገራችን በርካታ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ሃብት ያላት ሀገር መኾኗን ያነሱት ዋና አሥተዳዳሪው እነዚህን ሃብቶቿን እንዳትጠቀም ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጥረት ቢያደርጉም ኢትዮጵያ ያሏትን ፀጋዎች መጠቀም እንደምትችል ማሳየት መቻሉን አስረድተዋል።
በራስ አቅም በኅብረት ያሳካነው ግዙፍ ፕሮጀክት ነው በማለት በቀጣይ የሀገራችንን ብልጽግና እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅማችንን የሚያረጋግጡ በርካታ ስኬቶችን ለማስመዝገብ በትብብር ልንሠራ ይገባልም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን