በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የታየው አንድነት እና መተባበር በሌሎች የልማት ዘርፎችም ሊደገም ይገባል።

1

ደብረ ማርቆስ፡ መስከረም 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ እና አካባቢው ነዋሪዎች የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቅቆ ለምርቃት መብቃቱን ተከትሎ የድጋፍ ሰልፍ አካሂደዋል።

ደስታቸውን በአደባባይ በገለጹበት መርሐ ግብር ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ከጫፍ ጫፍ በይቻላል ስሜት አስደናቂ ትብብር ያሳዩበት ዳግም ዓደዋ ነው ብለዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የታየውን አንድነት እና ስኬት በሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶችም መድገም እንደሚገባ አመላክተዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የላብ እና የደም ዋጋ የተከፈለበት ድል ነው ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የትብብር እና የአንድነት ድምር ውጤት፣ የድህነት ቀንበርን የሰበረ የዳግም ዓደዋ ማሳያ የታሪክ አሻራ መኾኑንም አመላክተዋል።

በሕዝባዊ ትዕይንቱ ላይ የተሳተፉ የከተማዋ ነዋሪዎች ግድቡ በርካታ ፈተናዎችን ተሻግሮ ለፍፃሜ መድረሱ የተለየ ደስታ እንደፈጠረባቸውም ተናግረዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢኮኖሚያዊ ትሩፋት ይዞ የመጣ፣ አንድነት እና መተባበር በተግባር የታየበት የጽናት ተምሳሌት ነው ሲሉ አስተያየታቸውንም ሰጥተዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የታየው አንድነት እና መተባበር በሌሎች የልማት ዘርፎችም ሊደገም ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

መጭው ትውልድ አንድነት፣ ጽናት እና ጥንካሬን በመላበስ የራሱን ሀገራዊ አሻራ ማሳረፍ ይገባዋልም ተብሏል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article‎ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ ‎በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ላይ አርማጭሆ ወረዳ ትክል ድንጋይ ከተማ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄዷል። ‎
Next articleለኢትዮጵያ እድገት ወሳኝ በኾኑ ቁልፍ ልማቶች ላይ ልንተባበር ይገባል።