
ጎንደር: መስከረም 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የላይ አርማጭሆ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አስረሳው ደሴ ኢትዮጵያ የትልቅ ታሪክ ባለቤት መኾኗን አስታውሰው ታላቁን የሕዳሴ ግድብ በራስ አቅም ገንብቶ ማጠናቀቅ መቻሉ ትልቅ ድል መኾኑን አንስተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ ፈተናዎች ቢገጥሙትም የነፃነት አርማ የኾነችው ኢትዮጵያ በልጆቿ የጋራ ጥረት ለስኬት መብቃት መቻሏን አረጋግጠዋል።
የድጋፍ ሰልፉ ከቦንድ ግዥ ጀምሮ ድጋፍ ሲያደርጉ የቆዩ የወረዳው ነዋሪዎች በመጠናቀቁ የተሰማቸውን ደስታ እና አብሮነት ለማረጋገጥ የተካሄደ መኾኑንም ተናግረዋል።
ዋና አሥተዳዳሪው ኢትዮጵያን ወደ ቀደመ ከፍታዋ ለመመለስ አሁንም ቀጣይ ፕሮጀክቶች እንደሚያስፈልጓት አመላክተዋል።
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ መላው ኢትዮጵያውያንን በተስፋ ሲጠብቁት የኖሩ ትልቅ ስኬት መኾኑን የወረዳው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ለዘመናት ስንናፍቀው የነበረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዕውን ኾኖ በማየታችን ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል ሲሉም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዳግም ዓድዋ ነው ያሉት ነዋሪዎቹ ኢትዮጵያውያን በኅብረት በመቆም የማይቻል የሚመስለውን ሁሉ እንደሚቻል አረጋግጠናል ብለዋል።
በቀጣይም በአንድነት ትልልቅ ፕሮጀክቶችን እና ሀገራዊ እቅዶችን ለማሳካት ኀላፊነታችን እንወጣለን ሲሉም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ቃልኪዳን ኃይሌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን