
ደብረ ብርሃን: መስከረም 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዳሴ ግድቡ መጠናቀቁን ተከትሎ በደብረ ብርሃን ከተማ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተደርጓል፡፡
ኢትዮጵያውያን በብዙ ውስብስብ ችግር ውስጥ ኾነን የዘመናት ህልማችንን በራሳችን አቅም እውን ያደረግንበት ነው ብለዋል የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች፡፡
ኢትዮጵያውያን ባለፍንባቸው የታሪክ ምዕራፎች ዓባይን ስንወቅስ ኖረናል ያሉት ተሳታፊዎቹ ያ የቁጭት ዘመን አቅም ኾኖን ይሄው ዛሬ ላይ የአንድነታችን ማስተሳሰሪያ የጋራ ግዙፍ ፕሮጀክት እንድናጠናቅቅ አስችሎናል ነው ያሉት፡፡ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከፕሮጀክት ጀምሮ እስከ ማጠናቀቅ የተሻገረ ትርጉም እንዳለውም ነዋሪቹ ገልጸዋል፡፡
“በኃይል አቅርቦት ለምትፈተን ሀገር እና ጨለማን ለሚታገል ሕዝብ” በራሱ ተፈጥሯዊ ሃብት ተጠቅሞ ችግሩን በውስጥ አቅም መፍታት እንደሚችል ያመላከተ ሕያው ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡
ግድቡን ስንጀምር አንስቶ በርካታ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጫናዎች እንደነበሩ ያስታወሱት የሰልፉ ተሳታፊዎች ትክክለኛ የልማት ትልም ወጥነን እንደ ሀገር ለተግዳሮቶች ባለመበገር ጥበብ በተሞላበት መንገድ ጫናው የታለፈበት ሂደትንም የሰልፉ ተሳተፊዎች አድንቀዋል፡፡
ፍጻሜው ላይ አተኩረን ግድቡን ገድበናል፤ ዓባይንም ለሀገሩ ባለውለታ አድርገነዋል ብለዋል ሰልፈኞቹ።
ዘጋቢ:- በላይ ተስፋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
