የግድቡ መጠናቀቅ የአሸናፊነት ድል አክሊልን መድፋት ነው።

2

ሁመራ፡ መስከረም 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁን ተከትሎ በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተሳተፉት የሁመራ ከተማ ነዋሪዋ ሕሪያ አብዱ “የዓባይ ግድብ መጠናቀቅ ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካውያንን ለልማት አነሳስቷል” ሲሉ ገልጸዋል። የዓባይ ግድብ ዕውን መኾን በዓለም ላይ በተረጅነት ስሟ ይነሳ የነበረችውን ሀገራችን ክብር ከፍ ያደርጋልም ነው ያሉት።

ዓባይ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ዓድዋ መኾኑን ያነሱት ደግሞ ሌላኛው የሰልፉ ተሳታፊ ሙሉጌታ ጥሩነህ ናቸው። የሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ የአይቻልም መንፈስ የተሰበረበት ነው ብለዋል።

የሕዳሴው ግድብ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት፣ ፍቅር እና መተባበር የታየበት ታላቅ የድል ታሪክ መኾኑን የሃይማኖት አባቶች እና የሃገር ሽማግሌዎች በዕለቱ ተናግረዋል።

የሕዳሴው ግድብ በመሪዎች ቁርጠኝነት ለድል የበቃ የኢትዮጵያውያን ኩራት ነው ሲሉ የገለጹት ደግሞ የሰቲት ሁመራ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ እንኳየነህ ሙሉ ናቸው።

ዓባይ በራስ አቅም እና መተማመን መገንባት መቻሉ የሕዝባችንን እና የመንግሥታችንን አሸናፊነት ለዓለም ያሳየነብት ነው ብለዋል።

የሕዳሴ ግድቡ ዕውን መኾን ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማት የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው ያሉት ደግሞ የዞኑ ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ምክትል ኀላፊ እና የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ ተወካይ ጌታቸው ሙሉጌታ ናቸው።

የሕዳሴው ግድብ በመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ትብብር እና ተሳትፎ ተገንብቶ መጠናቀቁ ለሀገር አንድነት እና እድገት የጎላ ሚና አለው ብለዋል።

“የግድቡ መጠናቀቅ የአሸናፊነት ድል አክሊልን የመድፋት ያክል ነው ፤ ግድባችን በራስ አቅም የተገነባ እና ለኢትዮጵያውያን ኩራት ነው፤ የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያ ማንሠራራት ምልክት ነው የሚሉት በዕለቱ በሰልፈኞቹ የተስተጋቡ መልዕክቶች ናቸው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleእንደ ሀገር የበለጸገ ማኅበረሰብ ለመፍጠር በሚደርገው ጉዞ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ወሳኝ ነው።
Next articleታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን በማስመልከት በመርጡለ ማርያም ከተማ የድጋፍ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።