
ደብረ ብርሃን፡ መስከረም 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያውያን በዓደዋ ድል በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ለነበሩ የአፍሪካ ሀገራት የነፃነት ቀንዲልን እንዳበሩ ሁሉ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቀኝ ግዛት ውልን የበጣጠሰ፣ የይቻላል መንፈስን የተላበሰ የዚህ ዘመን አርማ ነው ሲሉ የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ተናገረዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በውስጥም በውጭም ያጋጠመውን ፈተና በማለፍ የመጨረስ አቅም በተግባር የታየበት ነው ብለዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለመላው ጥቁር አፍሪካውያን ምልክት በመኾን ዳግማዊ ዓደዋ የተበሰረበት እንደኾነም አስረድተዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንደ ሀገር የበለጸገ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ለሚደረገው ጉዞ የሚወሰን የልማት ሁሉ ዐይን መግለጫ ነው ብለዋል።
እንደ ሀገር የሚሰተዋለውን የኀይል እጥረት ችግር ከመፍታ አልፎ ኢኮኖሚን በማሻሻል መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍ የሚደረገውን ጉዞ ያፋጥናል ነው ያሉት፡፡
የዘመናት የኢትዮጵያ መሪዎች እና ሕዝቦች ህልም የተመለሰበት የዚህ ትውልድ የአንድነት አሻራ መኾኑንም አንስተዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በላብ እና ደም በትውልድ ቅብብሎሽ የተሳካ ድል መኾኑን የገለጹት አቶ በድሉ የደብረ ብርሃን ከተማን ባለ አቅም ሁሉ ተረባርቦ ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ተመራጭ ለማድረግ በትኩረት መሥራት ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር ነው ብለዋል፡፡
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
ዘጋቢ፦ብርቱካን ማሞ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን