
ሰቆጣ: መስከረም 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ተከትሎ በመላው አማራ ክልል የደስታ መልዕክቶች እየተላለፉ ነው። በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችም ድጋፋቸውን በሰላማዊ ሰልፍ አሳይተዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ተገኝተው ደስታቸውን የገለጹት የሰቆጣ ከተማ ነዋሪው መሰለ ሚሰው ሕዳሴ የዘመኑ አድዋ መኾኑን እና ለልጅ ልጅ የሚነገር ታሪክ ነው ብለዋል። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአሸናፊነት ማሳያ እንደኾነም ገልጸዋል።
በቀጣይም እንደ ሀገር የታቀዱ የልማት ሥራዎችን እንደ ዓባይ በ14 ዓመት ሳይኾን በአጭር ዓመታት ለማሳካት እንሠራለን፤ እንደግፋለን ነው ያሉት።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ ወርቅ ተሾመ ለዓመታት የተደከመበት የልማት ውጤት በድል ሲጠናቀቅ እንደማየት ትልቅ ነገር የለም ብለዋል። ከመቀነታችን ፈትተን የለገስነው ሳንቲም ተደምሮ ጉባ ላይ ትልቅ ግድብ መኾኑ የመተባበርን ውጤት የሚያሳይ እና ትንሽ ድጋፍ ሲጠራቀም ትልቅ ለውጥ እንደሚሰጥ ያረጋገጠ ግድብ ነው ብለዋል።
በሰቆጣ ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጌትነት እሸቱ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአትችሉምን ትችት የቀየረ፤ የዘመናት የቁጭት ሥነ ቃሎችን የቀየረ፤ የይቻላል ማሳያ እንደኾነ ነው የገለጹት።
“ኢትዮጵያ ችላለች፤ የቻልነውም እኛ ነን” በቀጣይም በይቻላል ወኔ ችለን እናሳያለን ነው ያሉት። ኢትዮጵያውያን ሲተባበሩ ዓለምን የሚያስገርም ታሪክ የሚሠሩ መኾናቸውን ዳግም ያሳዩበት ከአድዋ ቀጥሎ ትልቁ የታሪክ አሻራ ነው ሲሉ ገልጸውታል።
ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ለብቻ መጠቀምን ሳይኾን አብሮ መበልጸግን የሚያስተምር ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ለዓባይ ተፋሰስ ሀገራትም የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ እና ኢትዮጵያም የራሷን ሃብት የመጠቀም መብቷን ያረጋገጠ ግድብ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
