
ጎንደር፡ መስከረም 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው እንደ ሕዝብ ቀና ያልንበት ዳግማዊ ዓደዋ የኾነው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለምርቃት መብቃቱ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።
ጨርሰነዋል፤ መረቅነዋል፤ እንደምንችል አሳይተናል ሲል የጎንደር ሕዝብ ደስታውን ለማሳየት አደባባይ መውጣቱንም ገልጸዋል።
ዓባይ ትናንት ትንቢት እና ተስፋ የነበረው ዛሬ ዕውን ኾኗል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ዓባይ ተገድቧል ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አፍሪካውያን ጫና ውስጥ ኾነው ስኬትን ማስመዝገብ እንደሚችሉ የሚያሳይ መኾኑንም ተናግረዋል።
አሸንፈን አፍሪካን አኩርተናል፤ ዓለምንም አስደምመናል ብለዋል። ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አክለውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሕዳሴ ግድቡ እንዲጠናቀቅ ላሳዩት ቁርጠኝነት አመሥግነዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አንድነት እና መተባበርን በተግባር ያሳየ መኾኑንም አብራርተዋል።
በጦርነት እና በግጭት ሀገር አይቀየርም ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ኅብረት እና አንድነት እንዲጠበቅ ሰላምን ማጽናት የሚገባ በመኾኑ ሁሉም ለሰላም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን