የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾን የአፍሪካ ኩራት እንደኾነ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

13

ጎንደር፡ መስከረም 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምርቃትን ምክንያት በማድረግ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ደስታቸውን በሰላማዊ ሰልፍ እየገለጹ ይገኛሉ።

ነዋሪዎቹ የተለያዩ ዜማዎችን፣ ጭፈራዎችን እና መልዕክቶችን በማስደመጥ ደስታቸውን እየገለጹ ነው።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ማድረግ እንደምንችል ማሳያ ነው ያሉት የከተማዋ ነዋሪ አቶ ይበልጣል ይርጋ ግድቡ አንድነት የታየበት የስኬት በር ነው ብለዋል።

ግድቡ እንዳይሠራ ጫና ይደረግ እንደነበር ያነሱት ነዋሪዎች ጫናዎችን በመቋቋም እና አብሮነትን በማጠናከር ዕውን ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

የሕዳሴ ግድቡ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾን የአፍሪካ ኩራት መኾኑንም ገልጸዋል።

በግድቡ መጠናቀቅ ደስተኛ መኾኑን የገለጸው ወጣት ሻምበል ጌታሁን በበኩሉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ መተባበርን ያሳየበት ነው ብሏል።

ወጣት ሻምበል ጌታሁን “ግድቡ ጀምረን እንደምንጨርስ ያሳየንበት የኢትዮጵያ ትንሳዔ ነው” ብሏል።

የዓባይ ግድብ የማንነት ማሳያ እና የነጻነት ነጸብራቅ በመኾኑ መጠናቀቁ ደስተኛ አድርጎናል ነው ያለው።

“ተማሪ እያለሁ ቦንድ በመግዛት ለዓባይ ግድብ የበኩሌን ድጋፍ አድርጌያለሁ” ያለችን የጎንደር ከተማ ነዋሪዋ ቤተልሔም ማናየ በግድቡ መጠናቀቅ ደስተኛ እንደኾነች ገልጻለች።

ግድቡ የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያሳይ እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን የሚያሳድግ መኾኑንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጅማሮ
Next articleየሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ምልክት ነው።