
ባሕር ዳር: መስከረም 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሥራ እና ክህሎት ቢሮ ሠራኞች የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መመረቅና ወደሥራ መግባቱን ተከትሎ የፖናል ውይይት አድርገዋል። የቢሮው ኀላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) እንደቢሮ በተደረገው የጋራ የደስታ መግለጫ እና ውይይት ላይ ተገኝተው ግድቡ ትርክትን የቀየረ ድል መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ የምትታወቀው በስደት፣ በርሃብ እና በቸነፈር ነበር ያሉት ኀላፊው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጠላቶች ሳይቀር ዐይናቸው ተገልጦ ኢትዮጵያ ማህጸነ ለምለም ሀገር መኾኗን የመሰከሩበት ነው ብለዋል፡፡
“ከተበባበርን ጠላቶቻችንም ቢኾኑ ስለእኛ የሚመሰክሩ እንደኾነ አረጋግጠናልም” ነው ያሉት፡፡ ይህም የኢትዮጵያውያን የአንድነት ውጤት መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ “አንድ ከኾን ሁሉም ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ አለ፤ የማይኾን ነገር የለም፤ እኛ ያጣነው ፍቅር ነው” ብለዋል፡፡
“ኢትዮጵያ የተስፋ ምድር ናት” በሚል ርዕስ ለተቋሙ ሠራተኞች የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) ኢትዮጵያውያን ከዓባይ ወንዝ ጋር ያላቸውን ቁርኝት፣ ዓባይ ወንዝ ላይ የአፍሪካ እና የዓለም ሀገራት ያላቸውን አተያይ፣ የኢትዮጵያ መሪዎች የዓባይ ወንዝ መገደብ ላይ ያበረከቱት አስተዋጽኦ፣ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ሊሠራቸው ያሰባቸው ሥራዎች እና ተያያዥ ጉዳዮችን በጹሑፋቸው ዳስሰዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከዓድዋ ድል ቀጥሎ ሁለተኛው ድል ነው ያሉት ኀላፊው ግድቡ በትብብር እንደተገደበው ሁሉ በቀጣይ በሚሠሩ ሌሎች ትልልቅ ፕሮጀክቶች ሁሉም በጋራ ክንድ ተባብሮ ለፍጻሜ ማድረስ እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አማረ አለሙ የ2018 አዲሱ በጀት ዓመት የተለየ ድባብ ይዞ የመጣ ዓመት መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ ድባብ በኢትዮያ ታሪክ ውስጥ በአስከፊ እንጉርጎሮ ይገለጽ የነበረውን የዓባይ ሁኔታ የቀየረ ነው ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በርካታ ውጣ ውረዶችን ካሳለፈ በኋላ በ2018 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ግድቡ ተጠናቅቆ ለኢትዮጵያውያን የደስታ ምንጭ በመኾኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
2018 ዓ.ም ዳግም የዓደዋ ድል በዓል የሚከበርበት ዓመት ነውም ብለዋል፡፡ ለኢትዮጵያውያን ብቻም ሳይኾን ለመላው አፍሪካውያን ኩራት እና የዕድገት መስፈንጠሪያ ድልድይ ይኾናል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ብዙ ትርጉም ያለው ነው ያሉት ምክትል ኀላፊው ዋናው ነገር የአንድነት ምሳሌ በመኾኑ በቀጣይ አንድ ኾኖ ለመቆም የሚያስችል ነውም ብለዋል፡፡ ዓባይ የደኅንነት፣ የኤሌክትሪክ እና የፋይናንስ ምንጭ ነውም ብለዋል፡፡
ዓባይ ኢትዮጵያውያን ከሃሳብ እስከ ገንዘብ በማዋጣት እንደማይለያዩ ያሳዩበት መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ቀጣይ ለሚሠሩ ፕሮጀክቶች ትልቅ አቅም እና ማስፈጸሚያ ስልት ኾኖ እንደሚያገለግልም ጠቅሰዋል፡፡
በፓናል ውይይቱ የተገኙት የአማራ ክልል አሠሪ እና ሠራተኛ ጉዳይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ስመኝ ዋሴ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በበርካታ ችግሮች ውስጥ አልፎ ለመመረቅ የበቃ፤ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ስኬት እና አቅም መኾን የቻለ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
የግድቡ መመረቅ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በፖለቲካ ዘርፉ ለሀገር እና ለማኅበረሰቡ በርካታ ጠቀሜታዎችን ይዞ የሚመጣ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ጥቁር ሕዝቦች መሥራት እና ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ ብሎም ከዚህ በኋላም ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደሚቻል ለዓለም ያሳዩበት ነው ብለዋል፡፡
ሠራተኞች ሠብሠብ ብለው ስለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውይይት ማድረጋቸው ቀጣይ ለሚሠሩ ፕሮጀክቶች በጋራ ኾኖ ለመንቀሳቀስ ያግዛል ነው ያሉት።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መመረቅን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን ከድህነት ለመውጣት በሚያግዙ እና ቀጣይ በሚሠሩ በርካታ ትልልቅ ፕሮጀክቶች በሚቻለው ሁሉ ሚናቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ሥራ እና ክህሎት ቢሮ አማካሪ ድረሴ እሸቴ የዓባይ ወንዝ አለመገደብ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ቁጭት ኾኖ መቆየቱን ጠቅሰው በመሪዎች አማካኝነት ፕሮጀክቱ ታስቦበት እና ተገንብቶ አሁን ላይ መመረቁ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ኩራት መኾኑን ተናግረዋል፡፡
የግድቡ መጠናቀቅ ሁለተኛ ድል ነው ያሉት አማካሪው “ግድቡ በበብዙ ተጽዕኖ አልፎ በራስ አቅም በይቻላል ስሜት ተገድቦ በመጠናቀቁ እንደ ሥራ እና ሥልጠና ክህሎት ቢሮ ሠራተኞች ደስታችን በጋራ ተካፍለናል” ብለዋል፡፡
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተገኘው ድል መነሻነትም መንግሥት በቀጣይ በርካታ ፕሮጀክቶችን ለመሥራት ዕቅድ ማቀዱን አብራርተዋል።
እንደ ግለሰብም በሚሠሩ ትላልቅ የልማት ሥራዎች ላይ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!