“ሕዳሴ ግድብ የኢኮኖሚያችን ተጨባጭ አቅም ነው” ጥላሁን መሐሪ (ዶ.ር)

1
ባሕር ዳር: መስከረም 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ የሥራ ኀላፊዎች እና ሠራተኞች የሕዳሴ ግድብ መመረቅን አስመልክተው የፓናል ውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ አካሄደዋል።
የአርቆ አሳቢና ትንቢታዊ ሕልም በሕዳሴ ግድብ እውን ኾኗል። ቀጣዩ ትውልድ በራሱ ነዋይ ይገነቡታል ያሉት የቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ምኞት ጉባ ላይ በዚህ ትውልድ ላይፋቅ ታትሟል። ሕልም ዘመናትን ተሻግሮ በታሪክ ሠሪ የዘመኑ ትውልዶች ገቢር ኾኗል። ሀገር ተረካቢ ትውልዶች እውነትም ቃላቸውን በአይበገሬነት አሳይተዋል።
አደራ ተብለው የነበሩት ዕድለኛ ትውልዶች ቃላቸውን አክብረዋል። ዓባይ አሁን የዜጎቹ ኩራት እና አቅም ነው።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ የታሪኩ ባለቤቶች ደስታቸውን በተለያዩ መንገዶች እየገለጹ ይገኛሉ። ለሌላ አኩሪ ድልም መነጋገር ጀምረዋል።
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ የሥራ ኀላፊዎች እና ሠራተኞችም የሕዳሴ ግድብ መመረቅን አስመልክተው የፓናል ውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ አካሄደዋል።
የውይይት መድረኩን የመሩት የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን መሐሪ (ዶ.ር) ናቸው። ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግድብ ብቻ ሳይኾን በብዙ መልኩ የሚተረጎም ነው ብለዋል። ሕዳሴ ግድብ ሕዝባችን እና ሀገራችን ወደ ተሰሚነት መድረክ ያመጣ የዘመኑ ስኬት እንደኾነ ነው የገለጹት ዶክተር ጥላሁን።
ግድቡ እኛ ኢትዮጵያውያን በዓለም መድረክ ላይ ከፍ ብለን እንድንታይም ዕድል የሰጠ ነው ብለውታል። ሀገራት ተደማጭ የሚኾኑት እና ዓለምን የሚዘውሩበት ምሥጢራቸው፣ የኢኮኖሚ ጉልበታቸው እንደኾነ የገለጹት ቢሮ ኀላፊው “ሕዳሴ የኢኮኖሚያችን ተጨባጭ አቅም ነው” ብለዋል። ኢትዮጵያ በዓለም ዐይን ውስጥ ገብታለች፤ ምክንያቷ ደግሞ ሕዳሴ ግድብ እንደኾነ ነው የገለጹት።
“ኢትዮጵያ የተስፋ ምድር” በሚል ርእስ ለተወያዮች የመነሻ ሰነድ ያቀረቡት በገንዘብ ቢሮ በኤጀንሲ ኀላፊ ደረጃ የማዕቀፍ እና ዓለም አቀፍ ግዥ ዳይሬክተር አያሌው አዛለ ናቸው። የግድቡ መጠናቀቅ ከተስፋ ብርሃን ወደ ተጨባጭ ብርሃን የተሸጋገርንበት ታሪካዊ አሻራ እንደኾነ በሰነዱ ላይ አመላክተዋል። መላው ኢትዮጵያውያን ለአንድ አላማ ተረባርበው ዳር ያደረሱት ትልቅ ፕሮጀክት ነው ሲሉ ነው የገለጹት።
ለሀገራችን ሉዓላዊነት እና የራስ የመቻል ትልቅ ማሳያም እንደኾነም በመወያያ ሰነዱ ላይ አንስተዋል። በሕዳሴ ግድቡ አንድነት ኀይል እንደኾነም የተማርንበት እንደኾነ ነው የገለጹት።
ዕድለኞች ኾነን ከግድቡ የመሠረት ድንጋይ እስከ ምረቃ ድረስ በማየታችን ደስተኞች ነን ሲሉ ተወያዮቹ ተናግረዋል። ሀገራዊ ልማት እና እድገት የቅብብሎሽ መኾኑንም በታላቁ የሕዳሴ ግድብ በተግባር አይተናል ነው ያሉት። ልጆቻችን የትም አይሄዱምና ለልጆቻችን ታሪክ አኑረናል፤ በዚህም ደስተኞች ነን ነው ያሉት ተወያዮቹ።
በቀጣይም አንድነታችን በማጠናከር ለሌሎች ልማቶች መነሳት ይኖርብናል ሲሉ ነው በአጽንኦት የገለጹት።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መሪዎች ጋር ተወያዩ።
Next articleየአማራ ሴቶች ማኅበር ለተጋላጭ ሴቶች እና ልጃገረዶች የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።