“የሕዳሴው ግድብ ያለአንዳች ልዩነት ቆመን ልንዘክረው የሚገባ የኢትዮጵያውያን የመቻል ምልክት እና ድል ነው” ተስፋሁን ዓለምነህ

1
ባሕር ዳር: መስከረም 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዳሴ ግድቡን መመረቅ ተከትሎ ኢትዮጵያውያን ደስታቸውን ሲገልጹ ሰንብተዋል። በግድቡ ግንባታ ወቅት ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦውን ሲያበረክት የኖረው የአማራ ክልል ሕዝብም የፕሮጀክቱ ሪቫን መቆረጡን ተከትሎ ደስታውን በተለያየ መንገድ እየገለጸ ይገኛል።
የአማራ ክልል አካባቢና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የክልሉ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን እና የጣና ሐይቅ እና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃ ኤጀንሲ ሠራተኞች በጋራ በመኾን የግድቡን መጠናቀቅ የተመለከተ የፓናል ውይይት አድርገዋል።
በፓናሉ መክፈቻው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል አካባቢና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ኀላፊ ተስፋሁን ዓለምነህ “የሕዳሴው ግድብ ያለአንዳች ልዩነት በጋራ ቆመን ልንዘክረው የሚገባ የኢትዮጵያውያን የመቻል ምልክት እና ድል ነው” ብለዋል።
ሕዳሴ ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር መኾኗን ያስመሰከረችበት፤ ይቻላል የሚለው መንፈስ በተግባር የተገለጸበት እና የኢትዮጵያውያን የዘመናት ሕልም ጊዜው ደርሶ እውን የኾነበት የእድገታችን ተስፋ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
የሕዳሴ ግድብ ምርቃት ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ያስጠበቀችበት፣ ለዘመናት ሲደርስባት የቆየውን ዘርፈ ብዙ ተጽዕኖም መክታ ድል ያስመዘገበችበት ነው ብለዋል። የትናንት አባቶቻችን የማይቻለውን ችለው የዓድዋ ድል ባለቤቶች እንደኾኑ ሁሉ ይህ ትውልድም ሕዳሴን ዕውን በማድረግ የራሱን ድል ጽፏል ነው ያሉት አቶ ተስፋሁን። ሕዳሴ በአፍሪካ ቀዳሚ፣ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውም ጥልቅ ነው ብለዋል።
ሕዳሴ ሁላችንንም በአንድነት የሚያስተሳስር፣ የሚያግባባ እና የትኛውንም ልዩነት ወደጎን ትተን በጋራ ቆመንም ልንደሰትበት የሚገባ የጋራ ስኬት ስለመኾኑም ጠቅሰዋል።
የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ የደስታ ምንጭ ሲኾን፣ አይችሉም ሲሉን ለነበሩት ደግሞ አንገት የሚያስደፋ ስለመኾኑም ገልጸዋል። ትርጉሙም ጥልቅ ነው ብለዋል። “ሕዳሴን በንግግር ብቻ መግለጽ አይቻልም” ያሉት አቶ ተስፋሁን በአካል ታይቶ የማይጠገብ የቱሪዝም ጭምር ሀብት ስለመኾኑም አመላክተዋል።
መሪዎች ያልፋሉ፣ ትውልድም ሄዶ ትውልድ ይተካል ሕዳሴ ግድብ ግን ለትውልዶች የሚተላለፍ ሀብት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኀላፊ የዝና ደስታ ሕዳሴ ግድብ እንደሀገር ድህነትን ለመዋጋት እና ለመበልጸግ ሁነኛ መሳሪያ ነው ብለዋል። ሕዳሴ ግድብ ዳግም አድዋ ነው፤ ድህነትን ለመዋጋት የቆመ የጋራ ሀብታችን እና ድላችን ነውም ብለዋል።
የሕዳሴ መመረቅ የኢትዮጵያውያን ድል እና ተስፋ ስለመኾኑም ገልጸዋል። የሕዳሴን ዘርፈ ብዙ ጸጋ መጠበቅ፣ መንከባከብ እና በጋራ ተጠቅሞ ማደግ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።
አስተያየታቸውን ለአሚኮ ከሰጡት የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል በአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ኮሚሽን የግብዓትና ግብይት ዳይሬክተር ዓለምዘውድ ስሜነህ ሕዳሴ ከፓለቲካ በላይ የኾነ የሀገር እና የሕዝብ ሀብት ነው ብለዋል። ሕዳሴ መጠናቀቁ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ያስደሰተ የመቻላችን ምልክት ነው ሲሉም ተናግረዋል። ግድቡ ውጣ ውረዶችን ተሻግሮ በኢትዮጽያውያን የተሠራ የኢትዮጵያውያን በረከት ስለመኾኑም አንስተዋል።
በአማራ ክልል አካባቢና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን የእቅድና በጀት ዝግጅት ክትትል ግምገማ ዳይሬክተር በፍታ ጤናው ሕዳሴ እናቶች ከመቀነታቸው ፈትተው፣ እኛም ከደመወዛችን ቀንሰን የሠራነው የመላ ኢትዮጵያውያን ሀብት ነው ብለዋል። ሕዳሴ ቀጣይ የሀገራችን የኀይል ተስፋ ነው፣ በተለይም የእናቶችን ኑሮ ቀላል ያደርጋል ብለዋል።
በመኾኑም መላ ኢትዮጵያውያን ለዚህ ግድብ መጠናቀቅ እንኳን ደስ ያለን ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በነገው ዕለት እንደክልል በሚካሄደው የአደባባይ የደስታ መግለጫ ላይም በመገኘት ድጋፋቸውን እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። ሕዳሴ የጋራ ደስታችን ነው፤ በጋራ መጠበቅ እና መጠቀምም ይገባናል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
Previous article
Next articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መሪዎች ጋር ተወያዩ።