
ደሴ: መስከረም 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የደሴ ስታቲስቲክስ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ መረጃ ለሚሰበስቡ ሠራተኞች ሥልጠና መስጠት ጀምሯል።
በ2018 ዓ.ም ከሚከናወኑ ዋና ዋና የስታቲስቲክስ ቆጠራዎች መካከል የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ አንዱ መኾኑን የደሴ ስታቲስቲክስ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ዑስማን ሙሐመድ ተናግረዋል።
ቆጠራው የሀገራችንን አሁናዊ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርትን የማወቅ ዓላማ መያዙን አስረድተዋል። በተጨማሪም የኢኮኖሚው ዘርፍ በክልል እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ነባራዊ መረጃ ማስገኘት መኾኑን ጠቅሰዋል።
ሥራው ኀላፊነትን እና ትጋትን የሚጠይቅ መኾኑን በመጥቀስ ሠልጣኞች ሥልጠናውን በንቃት እንዲከታተሉ ጠይቀዋል።
ከሥልጠናውም በኋላ ሥራቸውን በላቀ ሥነ ምግባር በማከናወን መረጃዎችን በትክክል እንዲሰበሰቡ አደራ ብለዋል።
ማኅበረሰቡም በቀናነት መረጃ እንዲሰጡ አሳስበዋል። ቆጠራውን ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የሥልጠናው ተካፋዮች ሥልጠናውን በንቃት በመከታተል እና ዓላማውን በመረዳት ትክክለኛ መረጃ ለመሰብሰብ ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የተጣለብንን ሀገራዊ ኀላፊነት በብቃት ለመወጣት እንሠራለንም ነው ያሉት። ሥልጠናው ከመስከረም 5 እስከ 29/2018 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።
ዘጋቢ:- መስዑድ ጀማል
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!