በምዝገባ የታየው ስኬት በትምህርት ወቅት እንዲደገም ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ ተጠየቀ።

2
ሁመራ፡ መስከረም 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የተመዘገቡ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት በመላክ ወላጆች ኀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ትምህርት መምሪያ አሳስቧል።
በዞኑ የ2018 ዓ.ም ትምህርት መሰጠት መጀመሩን ተከትሎ አሚኮ በትምህርት ቤቶች ተገኝቶ ምልከታ አድርጓል።
ለምለም አያሌው የሰቲት ሁመራ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ናት። አቤል ፈንታሁን ደግሞ የኅብረት አንደኛ መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነው።
ተማሪዎቹ ትምህርት ቀድሞ በመጀመሩ ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል። ሌሎች ተማሪዎችም መጥተው እንዲማሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ቀደም ብሎ ትምህርት መጀመሩ ተማሪዎች ማግኘት የሚገባቸውን እውቀት አግኝተው ለፈተና ብቁ እንዲኾኑ ያደርጋል ሲሉ የኅብረት አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር መከተ ጀንበሩ ተናግረዋል። ለዚህም መምህራን ዝግጅት አድርገው ወደሥራ መግባታቸውን አንስተዋል።
ትምህርት ቤቶቹ በተቀመጠው እቅድ መሠረት ትምህርት ማስጀመራቸውን የሰቲት ሁመራ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አሰፋ ባራኪ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ የተመዘገበው ተማሪ በሙሉ በማስጀመሪያው ቀን መገኘት እንዳልቻለ ነው ርዕሰ መምህሩ ያነሱት። የትምህርት መሸራረፍ እንዳይኖር ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ሊልኩ እንደሚገባ ርዕሰ መምህሩ ጠይቀዋል።
ትምህርት ቤቱ እና መምህራኑ ሙሉ ዝግጅት አድርገው ወደ ሥራ መግባታቸውን ያነሱት ደግሞ የኅብረት አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት የሻለም አየሁን ናቸው።
ሙሉ ተማሪው ወደ ትምህርት ቤት መጥቶ ካልተማረ የክፍለ ጊዜ መሸራረፍ ሊያጋጥም ስለሚችል ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊሠራ እንደሚገባ ርዕሰ መምህሯ ጠቁመዋል።
በምዝገባ ሂደቱ የተሻለ አፈጻጸም መኖሩን የዞኑ ትምህርት መምሪያ የእቅድ ዝግጅት ቡድን መሪ ሙላት አማረ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ የምዝገባውን ስኬታማነት በትምህርት ወቅት ለመድገም ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት በመላክ ወላጆች ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleለመካከለኛ እና ዝቅተኛ መሪዎች ሥልጠና እየሰተጠ ነው።
Next article