
ባሕር ዳር፡ መስከረም 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ሠራተኞች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ የፓናል ውይይት አካሄደዋል፡፡
በፓናል ውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ጀምራ መጨረስ እንደምትችል አቅም ያሳየችበት፣ በዓለም ዓደባባይ የመከራከር እና የመደራደር አቅሟን ከፍ አድርጎ ያሳየችበት ነው ብለዋል።
በዚህም ተሰሚነቷ ጎልቶ የወጣበት በመኾኑ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ትላልቅ ፕሮጀክቶችን መገንባት እንደምትችል ያረጋገጠ ነውም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ መንግሥት ፍትሃዊ የውኃ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ አቋማቸው ቢኾንም የታችኛው የናይል ተፋሰስ ሀገራት ግብጽ እና ሱዳን ዘመን ያለፈበት የቅኝ ግዛት ሥምምነትን በማንሳት ግድቡ እንዳይገደብ በርካታ ውንጀላዎችን ሲያቀርቡ እንደነበር አስታውሰዋል።
ዓለም አቀፍ ሕጎችን መሠረት ያደረጉ ሌሎች የልማት ሥራዎችን ለመሥራት ሕዝቡ መተባበር አለበት ብለዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እውቀትን፣ ፅናትን፣ አልሸነፍ ባይነትን እና አንድነትን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያስተማረ ዳግማዊ ዓድዋ ነው ሲሉም ገልጸውታል፡፡
የከፍታችን መገለጫ እና ከኢኮኖሚው በላይ በዲፕሎማሲው መስክ ያለንን ድርሻ ያሳደገ መኾኑንም ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!