የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለሁሉም የሚደርስ የንጋት ብርሃን ነው።

3
ባሕር ዳር: መስከረም 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኀበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሥራ መሪዎች እና ሠራተኞች የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃትን ምክንያት በማድረግ ውይይት አድርገዋል።
ለመወያያ መነሻ የሚኾን ጽሑፍም በቢሮው ምክትል ኀላፊ ንጹህ ሽፈራው ቀርቧል።
የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በትውልድ እና በመሪዎች ቅብብሎሽ ተገንብቶ መመረቁ ለኀብረተሰቡ ዘርፈ ብዙ ጥቅም፣ ለሀገሪቱ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት መስፈንጠሪያ እንደሚኾን ነው ሠራተኞቹ የተናገሩት።
በቢሮው የሰው ሃብት አሥተዳደር ዳይሬክተር ፈለቀች ፈንቴ የሕዳሴው ግድብ ተገንብቶ መመረቁ የሀገርን ከፍታ የጨመረ እና ገጽታን በአዎንታ የቀየረ በመኾኑ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ነው የተናገሩት።
ግድቡ በመመረቁ በተለይ ሴቶች ይደርስባቸው ከነበረው የማገዶ ጭስ ይታደጋቸዋል ብለዋል። የሥራ ጫናንም በእጅጉ ይቀንሳል የሚል ተስፋን እንዳላቸውም ጠቁመዋል።
ሀገር ስታድግ ሴቶችም በብዙ ዘርፍ ያድጋሉ ያሉት ወይዘሮ ፈለቀች የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በትውልድ እና መሪዎች ቅብብሎሽ ተገንብቶ መመረቁ ለኀብረተሰቡ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያስገኛል ነው ያሉት።
በቢሮው የግዥ እና ፋይናንስ ንብረት አሥተዳደር ዳይሬክተር ካሳየ ያለው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ መመረቁ ፋይዳው ለሁሉም የኀብረተሰብ ክፍል ቢኾንም ማገዶ በጀርባቸው ተሸክመው ኑሮን ለሚገፉት ሴቶች የተለየ አበርክቶ ይኖረዋል ነው ያሉት።
የግድቡ መመረቅ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የኤሌክትሪክ ውስንነትም በማስወገድ ረገድ ይዞት የመጣው ጥቅም ከፍተኛ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
“የገጠሩ ማኀበረሰብ ክፍል መቼ መብራት አግኝቼ ?”የሚለውን ጥያቄ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተገቢው ኹኔታ ይመልሰዋል ነው ያሉት። በመኾኑም ሌሊት በጨለማ ውስጥ ኾነው በጭስ እየታፈኑ ምግብ ማብሰልን ከማስቀረት ባሻገር ጤናንንም ለመጠበቅ የሚኖረው ጥቅም ከፍተኛ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኀበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን “ይቻላልን!” በተግባር ያሳዩበት የክፍለ ዘመኑ የጀግንነት ውጤት ነው ብለዋል።
እናቶች በመቀነታቸው የቋጠሩትን ብር ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መስጠታቸው ተትረፍርፏቸው ሳይኾን በችግር የጎበጠው ወገባቸው እንደሚቃና ተስፋ በማድረግ እንደኾነ ቢሮ ኀላፊዋ አስታውሰዋል።
ወይዘሮ ብርቱካን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መመረቅ የእናቶችን በጭስ የሚጠፋ ዐይን ይታደጋል ነው ያሉት። የትውልዱ የወደፊት እጣ ፋንታ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ትሩፋት እንደሚወሰንም ተናግረዋል።
ይህ ግድብ ለሕጻናትም የተለየ መልዕክት ይዟል ያሉት ወይዘሮ ብርቱካን የዓደዋን ድል ሲያስታውሱ ሌላም ዓደዋ እንዳለ ነጋሪያቸው ይኾናል ብለዋል።
አረጋውያንም ዓባይ ሳይገድብ የባዕድ ሀገር ሲሳይ ኾኖ በመቆየቱ የነበረባቸውን ቁጭት በመወጣት የታሪኩ ተካፋይ ስለኾኑ መደሰታቸውንም ነው ቢሮ ኀላፊዋ የተናገሩት።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አካታች እና ለሁሉም የኀብረተሰብ ክፍል የሚደርስ የንጋት ብርሃንን ይዞ እንደሚመጣ ወይዘሮ ብርቱካን ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበወልድያ ከተማ አስተዳደ ስር ባሉ 40 ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራ ተጀምሯል።
Next article“ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እውቀትን፣ ፅናትን፣ አልሸነፍ ባይነትን እና አንድነትን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያስተማረ ነው”