
ከሚሴ: መስከረም 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የ2018 የትምህርት ዘመን ትምህርት በሁሉም አካባቢዎች እንዲጀመር አቅጣጫ መቀመጡ ይታወቃል። ይህንንም ተከትሎ በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሉ ወረዳ እና ከተማ አሥተዳደር ትምህርት ቤቶች ትምህርት ተጀምሯል።
አሚኮ በደዋጨፋ ወረዳ በተረፍ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝቶ የመማር ማስተማር ሁኔታውን ቃኝቷል።
በትምህርት ቤቱ በመገኘት ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያገኛቸው ተማሪዎች የ2018 የትምህርት ዘመን ትምህርታቸውን በመጀመራቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል። በትምህርት ዘመኑም የተሻለ ውጤት ለማምጣት መዘጋጀታቸውን ነው የተናገሩት።
የትምህርት ቤቱ መምህራን እና ርዕሰ መምህራን በክረምት ወቅትም ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት ሲሰጡ መቆየታቸውን ጠቅሰው በትምህርት ዘመኑም ለተማሪዎች ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የደዋጨፋ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ተወካይ ኀላፊ አብዱ መሀመድ በወረዳው ከ25 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርት ጀምረዋል ብለዋል።
በወረዳው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በቀጣይ በቅንጅት እንደሚሠራም አሳስበዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ እንድሪስ አህመድ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ167ሺህ በላይ ተማሪዎች መመዝገባቸውን ገልጸው በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በ280 ትምህርት ቤቶች ላይ ትምህርት መጀመሩን አሥረድተዋል።
ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይኾኑ የአካባቢው ማኅበረሰብ ከ20 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ በማሠባሠብ ለተማሪዎች ማድረስ እንደተቻለም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!