
ደብረ ብርሃን: መስከረም 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማሩ የሚያስፈልጓቸውን ግብዓቶች በማሟላት የ2018 ትምህርት ዘመን በወቅቱ ማስጀመር መቻሉን የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ገልጿል፡፡
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ መቅደስ ብዙነህ ተማሪዎች ለመማር ማስተማሩ ቀጥተኛ እገዛ የሚያደርጉ ግብዓቶችን መንግሥት በራሱ ወጭ እና ከተለያዩ ባድርሻ አካላት በማሠባሠብ ለማመሏት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
በከተማ አሥተዳደሩ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለትምህርት ዘመኑ የሚያገለግሉ ተጨማሪ ስድስት የመማሪያ ብሎኮች መገንባታቸውን ኀላፊዋ ተናግረዋል፡፡
በከተመዋ ሁሉም ትህርት ቤቶች ዛሬ ትምህርት ተጀምሯል ነው ያሉት፡፡
በደብረ ብርሃን ከተማ የጠባሴ መድኃኒዓለም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ታደሰ በላቸው በትምህርት ቤቱ የተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስን ጨምሮ የተለያዩ እግዛዎች መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
ዛሬ በትምህርት ቤቱ የ2018 የመማር ማስተማር ዘመን መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡ በአቅም ውስንነት ምክንያት የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት ላልቻሉ ወገኖች በትምህርት ቁሳቁስ በኩል የተደረገው ድጋፍ በወቅቱ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ እንደሚያግዛቸው አሚኮ ያነጋገራቸው ወላጆች ጠቁመዋል፡፡
የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በከተማዋ በ119ኙም ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራው በተሻለ መንገድ እንዲከናወን ዝግጅቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው እንደገለጹት የትምህርት ቤቶችን ገጽታ መቀየር፣ በቂ የኾነ የሰው ኀይል መመደብ እና የትምህርት ቤቶችን የግብዓት ፍላጎት ማሟላት ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በ15 ትምህርት ቤቶች በባለፈው የተጀመረውን የምገባ መርሐግብር በዚህ ዓመት አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሠራ ነውም ብለዋል።
በቀጣይም አስፈላጊ ድጋፎችን በማድረግ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ወደ ተግባር እንዲገቡ ክትትል ይደረጋል ነው ያሉት አቶ በድሉ፡፡
ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ለማሟላት በተደረገው ጥረት ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት እገዛ መደረጉን ከከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ዘጋቢ፦ በላይ ተስፋዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!