
ደሴ: መስከረም 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በኮምቦልቻ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ትምህርት መጀመራቸው ተመልክቷል።
የኮምቦልቻ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ትሁት ግርማ ሞገስ እና ተማሪ ብሩክ ጥላሁን ክረምቱን በንባብ እና ለትምህርት ዘመኑ በመዘጋጀት ማሳለፋቸውን ተናግረዋል።
ለ2018 የትምህርት ዘመን በሁሉም ረገድ መዘጋጀታቸውን እና በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንዳቀዱ ማቀዳቸውንም ገልጸዋል።
መምህራን እና የወላጅ መምህራን ኅብረት አስተባባሪዎችም ለትምህርት ዘመኑ ውጤታማነት የሚጠበቅባቸውን ዝግጅት ማድረጋቸውን አስረድተዋል።
“ተማሪዎች የሞባይል ስልክ ይዘው ወደ ትምህርት ቤት እንዳይገቡ፣ የአለባበስ እና የፀጉር አቆራረጥ መመሪያን እንዲያከብሩ፣ እንዳያረፍዱ፣ ትምህርታቸውን በትኩረት እንዲከታተሉ አስገንዝበናል” ነው ያሉት።
የኮምቦልቻ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር በቀለ ወርቁ በትምህርት ዘመኑ በትምህርት ቤቱ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ከ1ሺህ 800 በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ይከታተላሉ ብለዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ መንግሥቱ አበበ በኮምቦልቻ ከተማ የግል ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚያስተምሩ 92 ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።
በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ከ43ሺህ በላይ ተማሪዎች በ2018 የትምህርት ዘመን ትምህርታቸውን ይከታተላሉ ብለዋል።
በዕለቱ በሁሉም የመንግሥት እና የግል ትምህርት ቤቶች ትምህርት መሰጠት መጀመሩንም የመምሪያው ኀላፊ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ከድር አሊ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!