
ባሕር ዳር: መስከረም 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ቤቶች ልማት ድርጅት የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ የፓናል ውይይት አካሂዷል።
የአማራ ክልል ቤቶች ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አሥኪያጅ አበረ ሙጬ እንዳሉት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ሲተባበሩ ታምር መሥራት እንደሚችሉ ያሳዩበት ነው።
ኢዮጵያውያን በውጭ ወረራ ወቅት ሀገራቸውን ላለማስደፈር ነጻነታቸውን እንዳስከበሩ ሁሉ አሁንም ታላቁ ጠላት የኾነውን ድህነትን ለማስወገድ የተረባረቡበት ዳግማዊ ዓደዋ መኾኑን ገልጸዋል።
አንድነትን፣ ጽናትን፣ አይበገሬነትን ያሳየ፣ የታሪካዊ ጠላቶችን ሴራ ደግሞ ማክሸፍ የተቻለበት መኾኑንም ነው የገለጹት። የመሪዎችን የዲፕሎማሲ ጥበብ፣ የሰጥቶ መቀበል መርህን፣ በጋራ መልማት እና መጠቀምን ያሳየ መኾኑንም ገልጸዋል።
አሁንም የውስጥ ችግሮቻችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ለጋራ ጥቅም መቆም ይገባል ብለዋል።
የአማራ ክልል ቤቶች ልማት ድርጅት
የአሥተደዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አሥኪያጅ ሷሊህ አቡ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከዚህ መድረስ እንዲሁ አልጋ ባልጋ አለመኾኑን ገልጸዋል።
የውጭ የፋይናንስ ተቋማት እና ድርጅቶች ላይ ጫና በመፍጠር እና የውስጥ ባንዳን ጭምር በማሰማራት ለማስተጓጎል የተደረገውን ጫና ፈንቅሎ በመውጣት እውን የኾነ ፕሮጀክት መኾኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ዘላቂ ዕድገት ለማረጋገጥ አሁንም ለዓባይ፣ ለሰላም እና ደኅንነት፣ ለባሕር በር፣ ለሳይንስ እና ቴክኖሎጅ፣ ለዲጂታላይዜሽን ትኩረት መስጠት ይገባል ብለዋል።
ሀገሪቱ በቀጣይ ለመተግበር ያቀደቻቸው የማዕድን ማውጣት፣ የአፈር ማዳበሪያ ግንባታ፣ የኒውክለር ፕላንት፣ ግዙፍ የአየር መንገድ ግንባታ እና መሰል ዕቅዶች ዕውን እንዲኾኑ እንደ ግድቡ ሁሉም መተባበር ይገባዋል ነው ያሉት።
ምክትል ዋና ሥራ አሥኪያጁ እንዳሉት በ2025 የአፍሪካ ተምሳሌት ሀገር እንድትኾን ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል። በክልሉም ከ2018 ዓ.ም ጀምሮ የሚተገበር የ25 ዓመት የአሻጋሪ ዕቅድ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ ተስፋሁን አራጋው እንዳሉት ግድቡ የሀገሪቱን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካ አቅም ያሳደገ፣ ብሔራዊ አንድነት የፈጠረ መኾኑን ተናግረዋል።
ግድቡ በሃሳቡ አመንጭዎች ብቻ ያልተጠናቀቀ፣ በፈጻሚውም ብቻ ያልተጀመረ በመኾኑ ሃሳቡን ካመነጩ የቀድሞ መሪዎች እና ባለሙያዎች ጀምሮ እስኪ ፈጸም ድረስ በገንዘብ፣ በጉልበት እና በሃሳብ ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ ሊመሠገኑ ይገባል ብለዋል።
ሌላኛው የውይይቱ ተሳታፊ እንግዳው ጠገናው እንዳሉት ደግሞ በኢትዮጵያውያን አንጡራ ሃብት ዕውን የኾነውን ግድብ ደኅንነቱን ማረጋገጥ ይገባል። ግድቡ በደለል እንዳይሞላ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ በተፋሰሱ ላይ የፌዴራል መንግሥት ጭምር ትኩረት ሠጥቶ መሥራት ይገባዋል ነው ያሉት።
አቶ ፍቅር መኮንን እንደገለጹት ደግሞ የሕዳሴው ግድብ በክልሉ በ25 ዓመቱ ስትራቴጂክ ዕቅድ የታቀዱ የልማት ሥራዎችን ለመገንባት ማሳያ ነው። የተቀመጡ ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች እውን እንዲኾኑ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር፣ የውስጥ ልዩነቶችንም በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!