
ባሕር ዳር፡ መስከረም 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ “ኢትዮጵያ የተስፋ ምድር” በሚል መሪ መልዕክት ከሠራተኞቹ ጋር ተወያይቷል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ደስታን እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ባለሙያ ይናገር ይላቅ የዓባይ ግድብ እንደ ግለሰብም ኾነ እንደ ሕዝብ ኩራትን የፈጠረ ነው ብለዋል።
የዓባይ ግድብ ከሃሳቡ ጥንስስ ጀምሮ ኢትዮጵያውያን የተረባረቡበት እና መጠናቀቁን ሲናፍቁት የኖረ መኾኑን አንስተዋል። በመጠናቀቁ ደስተኞች ነን ያሉት ባለሙያው ደስታችን የመነጨው ሃብታችን መጠቀም በመቻላችን ነው ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በሁሉም መልኩ ጠቀሜታን ይዞ እንደመጣም ተናግረዋል። በኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ሲፈጠር የነበረውን የኃይል አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ሁነኛ መፍትሔ እንደሚኾንም አንስተዋል። ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ ሕዝብን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ያስችላልም ብለዋል።
ሌላኛዋ ተሳፊ ወይዘሮ ያለምሰላም አብተው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያውያን ከደስታ በላይ መኾኑን ገልጸዋል። ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን አይደፈሬነታችን በድጋሜ ያሳየንበት ነው ብለዋል። የሕዳሴ ግድብ ዳግማዊ የዓድዋ ድል መኾኑንም ገልጸዋል። ሕዳሴ ለኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ዘርፉ ትልቅ ተስፋ መኾኑንም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አማካሪ ባየ አለባቸው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አንድነትን ያረጋገጠ፣ ነጠላ ትርክትን ትቶ የወል ትርክትን ያጠናከረ መኾኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያውያንን በኅብረ ብሔራዊነት ያስተሳሰረ፣ በአንድነት እንድንጋመድ ያደረገ፣ ከተስፋ ብርሃን ወደ ሚጨበጥ ብርሃን የቀየረ፣ ለሌሎች ድሎች እንድንነሳሳ ያደረገ ነው ብለዋል።
የሕዝብን ቁጭት የመለሰ መኾኑንም ተናግረዋል። ከዚህ በኋላ ለበለጠ ቁጭት መነሳሳት እንደሚገባ ገልጸዋል። ሕዳሴ ግድብ በውስጥ ያለውን ባንዳ እና በውጭ ያለውን ባዳ ያሳፈረ መኾኑን ተናግረዋል።
የአፍሪካ ግዙን ግድብ ገድቦ መጨረስ ቀላል ነገር አለመኾኑንም ገልጸዋል። ትውልዱ በቁጭት እና በወኔ ሌላ ደማቅ ታሪክ እንዲሠራ ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል። ሕዳሴ በኢትዮጵያውያን አቅም የተሠራ በመኾኑ ልዩ እና የሚያኮራ ነው ብለዋል።
ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና ራስን የመቻል ማሳያ መኾኑን ነው ያነሱት። ግድቡ ታስቦ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ፈተናዎች እንደነበሩበት የተናገሩት አማካሪው ኢትዮጵያ ግን ፈተናዎችን ሁሉ ተቋቁማ ግድቧን አጠናቅቃለች ነው ያሉት።
ሕዳሴ የይቻላል መንፈስን ያደረጀ፣ የጂኦ ፖለቲካዊ እና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታን የቀየረ፣ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ያላትን ተቀባይነት ከፍ ያደረገ ነው ብለዋል። ከሕዳሴው ግድብ አንድነት ኃይል እንደኾነ፣ ጽናትን፣ ይቻላልን፣ አይበገሬነትን፣ ካልጨከን እና ለመስዋዕትነት ካልተዘጋጀን ከደህንነት እንደማንወጣ አስተምሮናል ነው ያሉት። ግድቡ ለኢትዮጵያ ልዩ ስጦታ፣ ድል እና ድምቀታችን ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ተፈሪ ታረቀኝ አባቶቻችን በዓድዋ ላይ ታላቅ ታሪክ እንደሠሩ ሁሉ የእኛ ትውልድ ደግሞ ሕዳሴን አጠናቅቆ ታላቅ አሻራ አሳርፏል ነው ያሉት። ሕዳሴ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ድል መኾኑንም ገልጸዋል።
ሕዳሴ ከግድብ በላይ ነው ያሉት ምክትል ኀላፊው ራሱን ችሎ ብዝሃ ኢኮኖሚ መኾኑንም ገልጸዋል። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቱሪዝም፣ የግብርና፣ የኢንቨስትመንት፣ የኃይል አቅም መኾኑንም አንስተዋል። ለኢንዱስትሪ ዘርፉ ደግሞ ትልቅ በረከት መኾኑን ነው የገለጹት። በኢንዱስትሪ እና በኢንቨስትመንት ይታይ የነበረውን የኃይል መቆራረጥ የሚፈታ እንደኾነም ተናግረዋል።
የሕዳሴ ግድብ የዘመናት ቁጭታችንን ያሠርንበት፣ ሌላ ድል አድራጊነት የተነሳሳንበት ነው ብለዋል። ሕዳሴ በዓባይ ውኃ አትጠቀሙም ሲሉ የነበሩትን ድል የነሳ እና አንገት ያስደፋ ፕሮጄክት መኾኑንም ገልጸዋል።
ሕዳሴ ሌሎች ታላላቅ ፕሮጄክቶችን ለማለም እና ለማድረግ ትልቅ እድል የፈጠረ እንደኾነም አንስተዋል። ሕዳሴ አባቶቻችን ሲያልሙት የኖሩ፣ ነገር ግን በዘመኑ ያላሳኩት እና በልጆቻቸው የተሳካ ነው ብለዋል።
በሕዳሴ ግድብ ላይ ምንም አይነት ልዩነት እንዳልነበር የተናገሩት ምክትል ኀላፊው ሕዳሴ አንድ ያደረገ እና ያሰባሰበ መኾኑን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!