“የራሳችን አቅም መፈተሽ እና መተባበር ከቻልን እንደምንችል አይተናል” ኢብራሒም ሙሐመድ(ዶ.ር)

1
ባሕር ዳር: መስከረም 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ሠራተኞች እና የሥራ ኀላፊዎች “ኢትዮጵያ የተስፋ ምድር” በሚል መሪ መልዕክት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መመረቅን አስመልክተው የፓናል ውይይት በባሕር ዳር ከተማ አካሂደዋል።
“እኛ ዓባይን እንገንባ ብንል አቅም የለንም። የውጭ ወዳጅ ሀገራትንም እርዱን ብንል ግብጽን ላለማስቀየም ፈቃደኛ አይኾኑም። ቀጣዩ ትውልድ በራሱ ንዋይ ይገነባዋል። ጥናቱ በክብር ይቀመጥ” ይህ ዘመን ተሻጋሪ ታሪካዊ ንግግር የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትንቢታዊ አደራ የነበር ነው።
የያኔው አሻጋሪ መሪ ዕይታቸው ዕውነትም በዚህ ትውልድ ገቢር ኾነ። ቃል በተግባር ያለምንም መሸራረፍ ተከወነ። ያኔ ቀጣዩ ትውልድ ተብሎ የተነገረላቸው ያሁኑ ትውልድ ቃላቸውን አከበሩ። የማይፋቅ ታሪክንም ሠሩ።
የታሪክ ባለቤት የኾኑት የዚህ ዘመን ትውልድም የሕዳሴ ግድብ መመረቅን አስመልክቶ ደስታቸውን በተለያዩ መንገዶች እያስተላለፉ ይገኛሉ። ለሌላ ታሪክም የሚመክሩበት ዘመን ላይ ናቸው።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መመረቅን አስመልክቶ የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት የሥራ ኀላፊዎች እና ሠራተኞች “ኢትዮጵያ የተስፋ ምድር” በሚል መሪ መልዕክት የግድቡን መመረቅ አስመልክተው ዛሬ ውይይት አድርገዋል።
የፓናል ውይይቱን የመሩት የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሒም ሙሐመድ (ዶ.ር) “የራሳችን አቅም መፈተሽ እና መተባበር ከቻልን እንደምንችል አይተናል፤ ለዚህም ሁሉም ሊኮራ ይገባል” ብለዋል። ኢትዮጵያ ከዚህም በላይ ስኬት እንደሚገባት የታየበት ፕሮጀክት መኾኑንም ለተወያዮች ገልጸዋል።
ከግጭት አዙሪት መውጣት ከተቻለ እና ትውልዱ ታሪክ መሥራት የማይታክተው ከኾነ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በላይም ታሪክ መጻፍ ይቻላል ነው ያሉት። የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጠላቶች የሀገሪቱን ልማት ሊያስቆሙት እንደማይችሉ የታየበት ነው ብለዋል።
የባዕዳን ተጽዕኖ እንደተጠበቀ ኾኖ ግድቡ ዳር እንዳይደርስ የውስጥ ባንዳም ተጽዕኖ እንደነበረበት አስታውሰዋል። በቀጣይ ግን ሁሉም ዜጋ ወደ ውስጥ መመልከት እና አንድነትን መርሕ ማድረግ ይኖርበታል ነው ያሉት።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ እንደ ትውልድ ምን ትምህርት እንደሚሰጥ ማሰብ ይገባል ነው ያሉት ዶክተር ኢብራሒም። ችግሮችን ሁሉ በመመከት ዳር የደረሰው የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ የአይበገሬነት ማሳያ እንደኾነም ነው ቢሮ ኀላፊው የተናገሩት።
በቀጣይ ሀገሪቱ ለምታስባቸው ፕሮጀክቶች ከግድቡ ትምህርት መውሰድ መሠረታዊ ነገር ነውም ብለዋል።
“ኢትዮጵያ የተስፋ ምድር” በሚል ርዕስ የመወያያ ሰነድ ያቀረቡት የቢሮው የግብይት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኀላፊ አትክልት አሳቤ ናቸው። ግድቡ የመላው ኢትዮጵያውያን የላብ ውጤት እንደኾነ በሰነዱ ላይ አመላክተዋል። ቁጥር ሁለት ዓድዋ የተደገመበት ታሪካዊ ስኬት ነው ሲሉም አትተዋል።
ግድቡ የበሳል መሪዎች የመወሰን ብቃት ታይቶበታል ነው ያሉት። የዲፕሎማሲ ጥበብም በተግባር የታጀበበት ስኬት እንደኾነ ነው የገለጹት ምክትል ኀላፊዋ። የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ የፋይናንስ ምንጭ ሕዝብ እና መንግሥት የኾነ ደማቅ ታሪክ የተጻፈበት እንደኾነም ተናግረዋል።
የሕዳሴ ግድቡ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ የተስፋ ፈር የቀደደ እንደኾነ በተወያዮች ተነስቷል። በስኬቱም ከልብ እንደተደሰቱ በመድረኩ ተወያዮች በሰፊው አንስተዋል።
የዓባይ ጉዳይ የንግግር ብቻ ኾኖ አልቀርም በተግባር ተተርጉሟልም ነው ያሉት። ግድቡን ከዚህ ላደረሱ ሁሉ ምሥጋና እንደሚገባቸውም ተወያዮች በአጽንኦት አንስተዋል።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመኑ ትምህርት መጀመሩን ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
Next articleሕዳሴ ከግድብ በላይ ነው።