
ባሕር ዳር፡ መስከረም 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ በባሕር ዳር ከተማ ትምህርት ቤቶች ተጀምሯል።
አጀማመሩን በተመለከተም በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኀበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው የወተት በር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው ተመልክተዋል።
እንደ ክልል የባለፉትን ሁለት ዓመታት ጭምር 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ለማስተማር ታቅዶ የምዝገባ ሥራው ሢሠራ መቆየቱን ዶክተር ሙሉነሽ አንስተዋል።
ዛሬም በክልሉ ለማስጀመር በተያዘው መርሐ ግብር መሠረት ትምህርት በይፋ ተጀምሯል ነው ያሉት። አጀማመሩም ተስፋ ሰጭ መኾኑን ነው ያነሱት።
የትምህርት ሥራ በቀናት፣ በሰዓታት እና በደቂቃዎች የተከፋፈል በመኾኑ በጊዜው ልጆች ወደ ትምህርት ቤት መምጣት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል። ባለድርሻ አካላትም ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህ ዓመት የተማሪዎች ምገባም ትኩረት ተሰጥቶበት እየተሠራበት መኾኑን ጠቅሰዋል። የምገባው መርሐ ግብርም በተመሳሳይ ከዛሬ ቀን ጀምሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ.ር) ትምህርት ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሢሠሩ መቆየታቸውን አንስተዋል።
በዚህ መሠረትም ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ በሚገኙት ትምህርት ቤቶች ትምህርት መጀመሩን ገልጸዋል። በሁሉም ትምህርት ቤቶችም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት።
በባሕር ዳር ከተማ በወተት በር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የግብረ ገብ ትምህርት መምህር ፀሐይ አበበ ችቦ ለኩሰን ዛሬ ትምህርት ጀምረናል ብለዋል።
ዓመቱ ጥሩ ተጀምሯል ነው ያሉት። ከአምናውም የተሻለ ተማሪ መምጣቱን መምህርት ፀሐይ አንስተዋል። መምህራንም ለማስተማር ዝግጁ ኾነው ትምህርት አስጀምረዋል ነው ያሉት።
የወተት በር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የ2ኛ ክፍል ተማሪ አዲሱ ዘሪሁን በ2017 ዓ.ም 1ኛ ደረጃ መውጣቱን ገልጿል።
ተማሪ አዲሱ ትምህርት ሲዘጋ እንደሚጨንቀው እና ደስተኛ እንደማይኾን ነው የገለጸው። ምክንያቱ ደግሞ ትምህርቱን እና የሚያስተምሩ መምህራንን ስለሚወዳቸው እንደኾነ ነግሮናል።
ትምህርት ናፍቆት እንደነበር እና ዛሬ በመጀመሩም ደስተኛ መኾኑን የተናገረው ተማሪ አዲሱ በ2018 ዓ.ም አንደኛ ለመውጣት ጠንክሮ እንደሚማር ገልጿል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!