
ገንዳ ውኃ: መስከረም 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን የ2018 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራው በገንዳውኃ ከተማ በይፋ ተጀምሯል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ደሳለኝ አያና የጸጥታ ችግር ካለባቸው ትምህርት ቤቶች በቀር በሁሉም አካባቢዎች ዛሬ በይፋ ትምህርት ተጀምሯል ነው ያሉት። በዞኑ ከ140 በላይ ትምህርት ቤቶች የማስተማር ሥራውን እንደጀመሩ ኀላፊው ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት አንድም ተማሪ ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይኾን በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል። በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ለኾኑ ተማሪዎች ከትምህርት ውጭ እንዳይኾኑ የቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል ነው ያሉት።
ለትምህርት ጥራት መምጣት አንዱ ግብዓት ስለኾነ በተቻለ መጠን የግብዓት ችግር ለመፍታት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የቁጥር አንድ አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት መምህርት የሺራት ከተማ ዛሬ ትምህርት ለመጀመር ቅድመ ዝግጅቴን አጠናቅቄ መጥቻለሁ ነው ያሉት።
ከወዲሁ ተማሪዎች ጥሩ ውጤት እንዲያመጡ ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት ተዘጋጅቻለሁ ብለዋል።
ወላጆች ትምህርት የተጀመረ መኾኑን አውቀው ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኳቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
የገንዳውኃ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አበበች እያዩ ለልጆቼ ሚያስፈልገውን የትምህርት ቁሳቁስ አሟልቼ ወደ ትምህርት ቤት አምጥቻለሁ ነው ያሉት።
ያለፈውን ዓመት ትምህርት ሳይረሱት ቶሎ መጀመሩ ለልጆች ጥሩ እንደኾነ ወይዘሮ አበበች ገልጸው አልባሌ ቦታ ከመዋል ትምህርት ቤት መዋላቸው መልካም እንደኾነ አንስተዋል።
የሰባተኛ ክፍል ተማሪዎች ባህሩ ጌታ እና ረድኤት ምኅረት ትምህርት በመጀመሩ ደስተኛ መኾናቸውን ነግረውናል።
ለ2018 የትምህርት ዘመንም ከባለፈው ዓመት የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደተዘጋጁ ተማሪዎች ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!