በምዕራብ ጎጃም ዞን የ2018 የትምህርት ዘመን መማር ማስተማር ተጀምሯል።

1

ፍኖተ ሰላም፡ መስከረም 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ተማሪ ሐና ማርያም አለነ እና አፀደ መለሰ በፍኖተ ሰላም ከተማ 01 እና ባከል የመጀመሪያ እና መካከለኛ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ናቸው። ትምህርታቸውን ለመከታተል ትምህርት ቤት ነው ያገኘናቸው።

 

ተማሪዎች እንዳሉን ባለፉት ሁለት ዓመታት በአካባቢው ትምህርት በመቋረጡ ትምህርት ላይ ያለንን ሥነ ልቦና አኮስሶታል ብለዋል። አሁን ላይ ትምህርት በመጀመሩ ደስ ብሎናል ብለዋል።

 

ሌላው በዳሞት አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የኾነው አቤል መለሰ ደግሞ ትምህርት በመቋረጡ ጓደኞቹ ወደ ሌላ አካባቢ በመሄድ ከትምህርት ገበታ በመራቃቸው ተስፋ ቆርጠው እንደቆዩ ተናግሯል።

 

ይሁን እንጂ ተማሪዎቹ በዚህ ዓመት መማር ማስተማሩ ቀድሞ በመጀመሩ የትምህርት ተስፋቸው መለምለሙን እና ደስተኛ መኾናቸውን አንስተዋል።

 

አሁንም ቢኾን የተጀመረው ትምህርት ተጠናክሮ እንዲቀጥልላቸው ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

 

መምህር ስንታየሁ አበዋ በባከል የመጀመሪያ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር ሲኾኑ በግጭቱ ምክንያት በርካታ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ከመምጣት ወደ አልባሌ ቦታዎች በመሄድ ጊዜያቸውን ያሳልፉ እንደ ነበር አስታውሰዋል።

 

የተማሪዎች ጉዳይ የሁላችን በማድረግ መማር ማስተማሩ በተጠናከረ መንገድ እንዲቀጥል ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

 

በምዕራብ ጎጃም ዞን ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ360 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ርቀው መቆየታቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ የስጋት ደሴ ተናግረዋል።

 

በዚህ ዓመት ደግሞ 426 ሺህ 29 ሺህ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ እየተሠራ ቢኾንም እስካሁን 41 ሺህ 366 ተማሪዎች ብቻ ናቸው የተመዘገቡት።

 

እንደ ዞን እያጋጠመ ያለውን የትውልድ መቋረጥ በመረዳት ወደ ትምህርት ቤት ያልመጡትን ለመመለስ ሁሉም በቁጭት ሊሠራ ይገባል ነው ያሉት መምሪያ ኀላፊው።

 

አሁንም አጀንዳችን ተማሪዎች ወደ ትምህርት እንዲመጡ መኾን አለበት ብለዋል። ለዚህም ሁሉም በቁጭት ባለቤት መኾን ያስፈልጋል ብለዋል።

 

ወደ ትምህርት ቤት ያልመጡ ተማሪዎችን የመመለስ ሥራውም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የመምሪያ ኀላፊው ገልጸዋል።

 

በዞኑ የ2018 የትምህርት ዘመን ምዝገባ በተከናወነባቸው ትምህርት ቤቶች መማር ማስተማር ሥራው ተጀምሯል።

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቁጭት ውጤት የኾነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ፋይዳ ከፍተኛ ነው።  
Next articleበምዕራብ ጎንደር ዞን ትምህርት ተጀምሯል።