
ባሕር ዳር፡ መስከረም 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ፣ የእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት እና የግብርና ጥራት እና ደኅንነት ባለሥልጣን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ መመረቅን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)፣ የእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጋሻው ሙጨ (ዶ.ር) እና የግብርና ጥራት እና ደኅንነት ባለሥልጣን ኀላፊ ፈንታሁን ስጦታው ተገኝተዋል።
ውይይቱን የከፈቱት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ትውልድ ለዘመናት ሲመኘው የነበረው እና የቁጭት ውጤት የኾነው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለሀገሪቱ እና ለክልሉ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ዶክተር ድረስ ዓመቱ ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶችን ለመፈጸም ሰፊ የንቅናቄ ዕቅድ የሚያዝበት እንደኾነም ገልጸዋል።
የክልሉን ሕዝብ ከችግር ለማላቀቅ የ25 ዓመት ፍኖተ ካርታ እና የአምስት ዓመት ስትራቴጅክ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ለሥራ ዝግጁ ኾኗል ብለዋል።
በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለኢኮኖሚው ዕድገት ሞተር ኾኖ የሚቀጥለው ግብርና መኾኑንም ጠቅሰዋል። ግብርናውም በፍጥነት አድጎ ለኢንዱስትሪው ምሰሶ እንደሚኾንም ገልጸዋል። ለዚህም ልዩ ትርጉም ሰጥቶ መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት።
በዝግጅቱ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ዘጋቢ ፊልም ቀርቧል። “ኢትዮጵያ የተስፋ ምድር” በሚል መሪ መልዕክትም የፓናል ውይይት ተደርጓል።
የኢትዮጵያ የጦርነት ታሪክ ለድህነት እንዳጋለጣት፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግን ከድህነት ለመውጣት እና የዲፕሎማሲ አቅም እንደሚኾን፤ ለዚህም መላ ኢትዮጵያውያን ተረባርበው እንዳሳኩትም ተነስቷል።
ኢትዮጵያ ከድህነት ተላቅቃ ክብሯን ለማስጠበቅም የሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ እንደሚቀጥልም ተነስቷል። ሕዝቡም እንደ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁሉ በሙሉ አቅም መረባረብ እንደሚጠበቅበት ተወስቷል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይኾን የጥቁር ሕዝቦችን መቻል የሚያሳይ እና ኩራት መኾኑን ነው ተወያዮች የገለጹት።
ግድቡ በመጠናቀቁም መደሰታቸውን ነው አስተያየት ሰጭዎች የተናገሩት። በቀጣይም ከድህነት ለመላቀቅ በሚደረግ ትግል ኀላፊነታቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!