
ደብረ ብርሃን: መስከረም 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ መቅደስ ብዙነህ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ከ56 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተማር እቅድ ተይዟል ብለዋል። እስካሁንም 47 ሺህ ተማሪዎች ተመዝግበዋል ነው ያሉት።
ባለፈው ዓመት በከተማው 12 ትምህርት ቤቶች ባለማስተማራቸው ከ1 ሺህ 700 በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በዚህ ምክንያት ተማሪዎች እና ወላጆች በሥነ ልቦና ከመጎዳታቸው ባለፈ በዕድሜያቸው ማግኘት ያለባቸውን እውቀት ሳያገኙ እንዲቀሩ አድርጓቸዋል ብለዋል።
ዘንድሮ በከተማው ያሉት 119ኙም ትምህርት ቤቶች ምዝገባ አካሂደዋል ብለዋል ኀላፊዋ። የባከነውን ጊዜ ለማካካስ በከተማ አሥተዳደሩ ያሉ የትምህርት ተቋማት በቁጭት ለመሥራት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡
የ2018 የትምህርት ዘመን በከተማ አሥተዳደሩ ጠባሴ መድኃኔዓለም 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በይፋ ሲጀመር የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸትን ጨምሮ የአሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ለዓለም ለይኩን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!