ማኅበራዊ ሚዲያን ለበጎ ተግባር

2

ባሕር ዳር፡ መስከረም 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከቴክኖሎጂ መዘመን ጋር ተያይዞ ዋና የመገናኛ እና የመረጃ መለዋወጫ የኾነው ማኅበራዊ ሚዲያ የሰው ልጅን ሕይወት እያቀለለ ነው።

 

በአንጻሩ ለጥላቻ እና ጥፋትም ይውላል። በተለይም የሚዲያ ግንዛቤ አነስተኛ በኾነባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት የሚዲያው አገልግሎት ለጥፋት ሲጋለጥ ይስተዋላል።

 

ፌስቡክ፣ ዩቲዩብ፣ ቴሌግራም፣ ቲክቶክ፣ በስፋት ጥቅም ላይ የመዋላቸውን ያህል ጠቃሚ ሃሳቦችን በማንሸራሸር ችግርን ለመቅረፊያ ከመጠቀም ይልቅ ጥላቻን የሚሰብኩ እና ከባሕል እና ሥነ ምግባር ያፈነገጡ ልምምዶች ሲስተናገዱባቸው ይስተዋላሉ።

 

በማኅበራዊ ሚዲያ የሚንሸራሸሩ የጥላቻ መልዕክቶች፣ የግጭት ጥሪዎች፣ አሰቃቂ ወንጀሎችን የሚያሳዩ ምስሎች እና ሌሎችም ከስብዕና ያፈነገጡ መልዕክቶች ፈተና ኾነዋል።

 

በአንጻሩ ደግሞ ባይበዙም ማኅበራዊ ሚዲያን ለዕውቀት ልውውጥ፣ ለሰላም፣ ለመደጋገፍ እና ለችግር መቀረፍ ዓላማ የሚያውሉም አሉ።

 

መምህር ሞሀመድ አሚን ማኅበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ ከሚጠቀሙት መካከል ይጠቀሳሉ። መምህሩ ማኅበራዊ ሚዲያን በተለይም ፌስ ቡክን ችግረኛ ተማሪዎችን በትምህርት ቁሳቁስ ለመርዳት ይጠቀሙበታል።

 

መምህር ሞሀመድ የኅብረተሰቡ የመከባበር፣ የመተዛዘን እና የመረዳዳት እሴትን በማኅበራዊ ሚዲያ ለማስቀጠል እና ለመጠቀም እንዲቻል ያስተምራሉ። በጎ ሥራዎችን በመተግበርም ንቁ ተሳታፊ ናቸው።

 

እንደማሳያ በ2016 የትምህርት ዘመን ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ በተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ ከ40 ሺህ በላይ ሰዎችን አስተባብረዋል። ለበርካታ ተማሪዎችም ድጋፍ በማድረግ ያለ ችግር እንዲማሩ አድርገዋል። አሁንም በጎ ሥራዎችን አስቀጥለዋል።

 

ማኅበራዊ ሚዲያ አሉታዊም ኾነ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዳለው የጠቀሱት መምህር ሞሀመድ አጠቃቀሙ እንደ ሰዎች እንደሚወሰንም ገልጸዋል።

 

ማኅበራዊ ሚዲያ የተራራቁ እና የተረሳሱ ሰዎችን ለመልካም ሥራ በማገናኘትም አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው። ሁሉም ለበጎ በመጠቀም መተጋገዝ እና ሕይወትን ቀለል ማድረግ ይገባል ነው ያሉት መምህሩ።

 

መምህር ሞሀመድ በከፈቷቸው የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮችን አፍርተዋል። በጎ፣ ትምህርታዊ እና የንግድ ሥራ ትምህርትንም ያስተላልፉባቸዋል። ይህን በጎ ተግባርም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የተናገሩት።

 

“ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የማገኛቸውን በጎ ሃሳቦች ለጓደኞቼ እና ተከታይቼ አጋራለሁ፤ በጎ ላልኾኑት ደግሞ ምንም ዓይነት ምላሽ አልሰጥም፤ ይልቁንም ለካምፓኒው ሪፖርት በማድረግም ተቃውሞየን እገልጻለሁ፤ መልዕክቱ ሪፖርት ከበዛበትም ካምፓኒው እንዲጠፋ ያደርገዋል” ነው ያሉት።

 

ማኅበራዊ ሚዲያን ለበጎ ከሚጠቀሙት መካከል ሌላኛው ደግሞ የባሕር ዳር ነዋሪው አቶ ታዘባቸው ጣሴ ናቸው።

 

አቶ ታዘባቸው አሁን ላይ ሁሉንም ማኅበራዊ ሚዲያዎች ይጠቀማሉ። ለመማማር፣ ለመቀራረብ እና ለበጎ እየተጠቀመባቸው መኾኑን ገልጸዋል።

 

“አንዱ በሌላው ላይ ከመነሳሳት እና ከጥላቻ ይልቅ ማኅበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ ብናውል ተጠቃሚ እንኾናለን” ነው ያሉት አቶ ታዘባቸው። የተሳሳቱ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀሞችን አይቶ ማለፍ ብቻ ሳይኾን ተገቢ አለመኾኑን ማስተማር እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

 

ከዚህ በፊትም በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች ላይ ይሳተፉ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ታዘባቸው ዘንድሮም በፌስ ቡክ የመማሪያ ቁሳቁስ በማሠባሠብ ለ100 ተማሪዎች አድርሰዋል።

 

ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም በተራራቀ ቦታ የሚኖሩ ሰዎችን በማስተባበር መሥራታቸውንም ጠቁመዋል። ለመቄዶንያ ባሕር ዳር ቅርንጫፍ ለማገዝ እንደተጠቀሙበትም ነው ለአሚኮ የተናገሩት።

 

የማኅበራዊ ሚዲያው አየር ወንድም ከወንድሙ ለማጋደል እና ለማጨራረስ ተጨናንቆ በነበረበት ጊዜ ይህን ስሜት ወደ ሰላማዊ እና መረዳዳት ለመቀየርም መሥራታቸውን አብራርተዋል።

 

በቀጣይ ማኅበራዊ ሚዲያን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም መረዳዳትን ማስቀደም እንደሚገባም አስገንዝበዋል። አረጋውያንን በየጊዜው ከመመጽወት ቋሚ ገቢ የሚያገኙበትን ዕቅድ ከጓደኛቸው ጋር በመኾን እየሠሩ እንደሚገኙም አብራርተዋል።

 

ሰው አፍራሽ እና አሉታዊ ነገሮች ላይ የመሳብ አዝማሚያ እንደሚታይበት የገለጹት አቶ ታዘባቸው ለሰላማዊ እና ለበጎ ዓላማ የሚለቀቁ መረጃዎችን የማበረታታቱ ሁኔታ ደካማ መኾኑን ነው ያነሱት።

 

ይህንን የተሳሳተ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን ማስተካከል ያለበት ራሱ ማኅበረሰቡ ነውም ብለዋል። ከአፍራሽ መልዕክቶች መታቀብ ብቻ ሳይኾን በመቃወም ጭምር የማኅበራዊ ሚዲያ ልምድን ማስተካከል እንደሚቻል ነው የመከሩት። ኀላፊነት መውሰድ እና ቁርጠኛ መኾን እንደሚገባም ነው አቶ ታዘባቸው የገለጹት።

 

በጎ በጎውን ማሰብ እና መሥራት በማኅበራዊ ሚዲያው ሲለመድ ለሀገር ሰላም እና መረዳዳትን ያተርፋል ብለዋል።

 

ብዙም ወጭ የማያስወጣውን ማኅበራዊ ሚዲያ ለበጎ ዓላማ በመጠቀም ኅብረተሰቡ ከድህነት ለመላቀቅ ያለበትን ውጣ ውረድ ማቅለል የተማረ ሰው መገለጫ ስለመኾኑም ነው የተናገሩት። የወገኑ ችግር የሚያሳስበው ሰው በሀሰተኛ እና የጥላቻ መረጃ ግጭቶችን እየቆሰቆሰ እልቂትን አያባብስም፤ የአቅማቸውን ያህል ለበጎ የሚሠሩ ሰዎችንም ማበረታታት ኀላፊነት እና ሰብዓዊነት የሚሰማው ዜጋ ሥራ ነው ብለዋል።

 

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሕዳሴ የአብሮነታችን ዋስትና የቁጭታችን መቋጫ፣ የነገዋ ኢትዮጵያ ተስፋ ብርሃን ነው” አቶ ይርጋ ሲሳይ
Next articleየ2018 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ በደብረ ማርቆስ ከተማ ተጀመረ።