“ሕዳሴ የአብሮነታችን ዋስትና የቁጭታችን መቋጫ፣ የነገዋ ኢትዮጵያ ተስፋ ብርሃን ነው” አቶ ይርጋ ሲሳይ

2

ባሕር ዳር: መስከረም 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የታላቁ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ “እምርታና ማንሠራራት” በሚል መሪ መልእክት ውይይት አካሂደዋል።

በውይይቱ የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ “ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የአብሮነታችን ዋስትና የቁጭታችን መቋጫ፣ የነገዋ ኢትዮጵያ ተስፋ ብርሃን ነው” ብለዋል።

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ውስጣዊ አንድነትን ያጠናከረ፣ የወል ትርክትን የገነባንበት የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም በመደመር እሳቤ ያረጋገጥንበት ታላቅ ፕሮጀክት ነዉ ያሉት አቶ ይርጋ በዚህ የተገኘዉን ሁለንተናዊ ፋይዳውን በመገንዘብ እና በማስገንዘብ ለኢትዮጵያ ብልፅግና ማኅበረሰባችን በጋራ እንዲነሳሳ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በተለይም የባንዳና የባዳ ጥምረቶችን በማክሰም የሀገራችን ኢትዮጵያ የጅኦ ስትራቴጅአዊ ቁመና የተቀየረበትና የዲፕሎማሲ የበላይነትን ያረጋገጥንበት ነው ብለዋል።

ሕዳሴ ግድቡ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ፀጋ የያዘ የትውልድ ሃብት ነው ያሉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ብስራት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ኩራት ነው ያሉት የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ፍሰሃ ደሳለኝ ሕዳሴ ግድቡ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የላብና የደም ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።

የውይይቱን መነሻ ሃሳብ የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ሽታው አዳነ ማቅረባቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለሕዝብ ተጠቃሚነት እንደሚሠሩ ጀማሪ እና መካከለኛ መሪዎች ገለጹ።