
ደሴ: መስከረም 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዲ ኤም ቪ ፎር ደሴ የበጎ አድራጎት ማኅበር በደሴ ከተማ ለሚገኙ 1ሺህ 500 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
በውጭ ሀገር የሚኖሩ የደሴ ተወላጆች ድጋፉን እንዳደረጉ የገለጹት የማኅበሩ አሥተባባሪ ማዘንጊያ አበበ ናቸው። የድጋፉ ዓላማ በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ከትምህርት ገበታቸው የሚቀሩ ሕጻናትን በትምህርት ገበታቸው እንዲገኙ ማድረግ ነው ብለዋል።
ድጋፉ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደተደረገበት የገለጹት አሥተባባሪው ለ1ሺህ 500 ተማሪዎች እንዲደርስ ተደርጓል ነው ያሉት። በቀጣይም መሰል ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።
“ተማሪዎችን ማገዝ ሀገርን ማገዝ ነው” ፤ ትምህርት ላይ መሥራት በቀጣይ ሀገራችን የምትፈልገው አይነት የሰው ኃይል ላይ መሠረት ማኖር ነው ያሉት ደግሞ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ፍቅሩ አበበ ናቸው። ዲ ኤም ቪ ፎር ደሴ በትምህርት መስኩ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መኾኑን ገልጸው ለዚህም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በደሴ ከተማ 21 ሺህ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች መለየታቸውን ያነሱት አቶ ፍቅሩ ከተለያዩ ድርጅቶች 9 ሺህ ደብተር መሰብሰቡን ገልጸዋል። ይህም የትምህርት ቁሳቁሱ ድጋፍ ለሁሉም እንዲዳረስ ያደርጋል ብለዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው የተማሪ ቤተሰቦች ድጋፉን ያደረጉትን በውጭ ሀገር የሚኖሩ የደሴ ከተማ ተወላጆችን አመስግነዋል። በየዓመቱ የሚደረገው ድጋፍ በብዙ መልኩ እያገዛቸው እንደኾነም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- አበሻ አንለይ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!